ኢትዮጵያ የኤርትራና ጅቡቲን አለመግባባት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

46
አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 ኢትዮጵያ በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሸምጋይነት ሚናዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት በመንግስትና ዲያስፖራው መካከል ለዘመናት ነግሶ የቆየውን የጥላቻ ግንብ ያፈረሰ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ቀንድ ሰላም የኢትዮጵያን ሚናን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የጀመረችውን ዓይነት መልካም ግንኙነት ወደሌሎቹ የአካባቢው ሀገራትም እንዲስፋፋ የመሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎት አላት። በመሆኑም በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲነግስ ሁለቱን ሀገራት ለመሸምገልና ለማደራደር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት  የተሳካ እንደነበርም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል። በጉብኝቱ ወቅት በተዘጋጁት 20መድረኮች ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሰባ በላይ በውጭ የሚኖሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ምሁራን ተሳትፈዋል። "በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሚኒሶታ ከተሞች የተካሄዱት እነዚሀ መድረኮች የኢትዮጵያ ችግር የሚያሳስባቸው፤ ነገር ግን ከመንግስት ጋር ተራርቀው የቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገ ተግባር የተከወነባቸው ናቸው" ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ጉብኝቱ ላለፉት 27 ዓመታት ተለያይተው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አንድነት የፈጠሩበት፣ በዜጎች መካከል የነበረው መፈራራትና መቃቃር የተናደበት፣ ጥላቻ በአንድነትና በፍቅር የተለወጠበት ነው ሲሉም አቶ መለስ ጠቁመዋል። ጉብኝቱ ከሌሎች አካላት ጋርም የሁለትዮች ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ዙሪያ  ለመነጋገር አድል የፈጠረ ጭምርም ነው ተብሏል። ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሐምሌ 21 ቀን ሎስ አንጀለስ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን የኢትዮጵያ ቀን እንዲሆኑ በከንቲባዎቻቸው አማካኝነት መወሰኑ ሌሎች አገሮች ያላገኙት ፤ ኢትዮጵያ ግን ራሷን ለዓለም የምታስተዋውቅበት እድል መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም