ከቡናና ፍራፍሬ ሽያጭ በምናገኘው ተጨማሪ ገቢ ኑሯችን እየተሻሻለ ነው-በሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች

69
ወልድያ ሀምሌ 27/2010 ከቡናና ፍራፍሬ ሽያጭ በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ በኑሯቸው ላይ መሻሻል እያሳዩ መሆናቸውን በሰሜን ወሎ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች ገለፁ። በሀብሩ ወረዳ ቀበሌ 18 ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ እንድሪስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት  ከሰብልና የጓሮ አትክልት ልማት በተጨማሪ ቡናና ፍራፍሬ በማልማት ገቢያቸውን እያሳደጉ ነው ። በዚህ አመት ከቡና፣ ማንጎና ብርቱካን ሽያጭ ከ50 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በተለይም የተዳቀለ ዝርያ ያለውን የማንጎ ምርት በገበያ ላይ ተመራጭ በመሆኑ በቀጥታ ለነጋዴዎች በማስረከብ ተጠቃሚ ያደረጋቸው መሆኑን ገልፀዋል ። በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ አራት ነዋሪ አርሶ አደር ጌታቸው አበራ በበኩላቸው በአካባቢው "አላውሀ" የተሰኘ ወንዝ  በመጥለፍ  ቡና፣ ማንጎና ብርቱካን በማምረት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል ። "በዚህ አመት ብቻ  ከምርት ሽያጭ ካገኘሁት ገቢ ውስጥ ከ80ሺህ ብር በላይ በባንክ ቆጥብያለሁ " ብለዋል ። በሰብልና የወተት ምርት የቤተሰባቸውን ፍጆታ ለሟማላት ያስቻላቸው በመሆኑ ከቡናና ፍራፍሬ ሽያጭ ከሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ውስጥ አብዛኛውን በባንክ ተቀማጭ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል ። "በአዲሱ አመት በኤሌክትሪክ የሚሰራ የእህል ወፍጮ በመትከል የገቢ ዘርፌን ለማስፋትና ህብረተሰቡንም ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ" ሲሉም ተናግረዋል ። "በመስኖ በመታገዝ የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጀሁ ከአካባቢው አልፎ ለአጎራባች ክልል ወረዳ ነዋሪዎች በሽያጭ በማቅረብ በማገኘው ገቢ በኑሮየ ላይ ለውጥ እያመጣሁ ነው " ያሉት ደግሞ በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ ስምንት ነዋሪ አርሶ አደር ደርቤ አባተ ናቸው ። በበጋው ወቅት የዘጋጇቸውን 37ሺህ የተዳቀለ ማንጎ፣ አቦካዶና ፓፓያ ችግኞች ከዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ አንዱን እግር በአማካኝ በ60 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ሞገስ ሙሉየ እንደገለፁት በዞኑ 17ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮች በቡናና ፍራፍሬ ልማት እየተሳተፉ ናቸው ። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዞኑ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቡናና ፍራፍሬ ምርት ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል። በዞኑ 5ሺህ  ሄክታር መሬት በቡናና ፍራፍሬ ልማት መሸፈኑን የገለፁት ባለሙያው በተያዘው ክረምት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን  ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም