መንግስት የፈቀደልን የመዋቅር ማሻሻያ ተግባራዊ ባለመሆኑ ቅሬታ ፈጥሮብናል—የሀረሪ ገቢዎች ባለስልጣን ሠራተኞች

1067

ሐረር ሀምሌ 27/2010 የሐረሪ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ሠራተኞች መንግስት የፈቀደላቸው የመዋቅር ማሻሻያ ለሁለት ዓመት ተግባራዊ ባለመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገለፁ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የባለስልጣኑ ሠራተኞች እንዳሉት በባለስልጣኑ የተሰራው የመዋቅር ማሻሻያ ለሁለት ዓመት ተግባራዊ አለመደረጉና ደመወዛቸው አለመሻሻሉ በሥራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል።

በባለስልጠኑ የታክስ መረጃ ቴክኖሎጂ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሄኖክ ደስታ ለኢዜአ እንደገለጹት በፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የመዋቅር ማሻሻያ መሰረት ተቋማቸው የራሱን ማሻሻያ ቢያደርግም ተግባራዊ አለመደረጉ ቅሬታ አሳድሮባቸዋል።

ይህም በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌሎች ክልሎች ተግባራዊ የሆነው የገቢዎች ባለስልጣን የመዋቅር ማሻሻያ በክልሉ ተግባራዊ አለመሆኑ ቅር እንዳሰኛቸውና አግባብ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ሐሰነት አባስ ናቸው።

መንግስት ለሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች በ2009 በጀት ዓመት ያደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ለተቋሙ ሠራተኞች እንዳልተደረገ የገለፁት ባለሙያው ሁኔታው በእርሳቸውና በሌሎች ሠራተኞችም የሥራ ተነሳሽነት ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ገልፀዋል።

በተቋሙ የውስጥ ኦዲተር ሠራተኛ ወጣት ነኢማ ሳዶ በበኩሏ “ የመዋቅር ማሻሻያው ተግባራዊ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ በማጣታችን የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል” ብላለች ።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ካሊድ አብዲ  ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  በሰራተኛው የተነሳው የመዋቅር ማሻሻያና የደመወዝ ጥያቄ  ተገቢነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

“የክልሎችን ተሞክሮ ከክልሉ አሰራር ጋር በማዛመድ የመዋቅር ማሻሻያ ቢሰራም በክልሉ ካቢኔ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ማሻሻያው ተግባራዊ ሳይሆን መዘግየቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር የገቢዎች ባለስልጣን የሰራውን የመዋቅር ማሻሻያ በቀጥታ በክልሉ እንዲተገበር ለካቢኔና ለሚመለከተው የመንግስት አካል መቅረቡን የገለፁት አቶ ካሊድ የሠራተኛው ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል

የሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ ካቢኔ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ዘከርያ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለካቢኔው የቀረበው የመዋቅር ማሻሻያ ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን አታሰዋል።

የአማራ ክልልን ገቢዎች ባለስልጣን የመዋቅር ማሻሻያ መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል የቀረበው የመዋቅር ማሻሻያ በክልሉ የሚሰበሰበውን ገቢ ተጨባጭ ያላደረገና የተጋነነ በመሆኑ ካቢኔው እንዳልተቀበለው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን መዋቅር ማሻሻያ ለካቢኔው መቅረቡንና ይህም ያልተጋነነ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፣ ካቢኔውም በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሰጠበትን የጸጥታ ሥራ እንዳጠናቀቀ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለጥያቄያው ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።