በምርጫው ካሸነፉ የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራና የፖለቲካ ተሳትፎ ችግርን መፍታት በልዩ ትኩረት የሚሰሩበት መሆኑን ፓርቲዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2013(ኢዜአ)በስድስተኛው ሀገርአቀፍ ምርጫ ካሸነፉ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በስራ እድል ፈጠራና የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን ችግር የመፍታት አማራጭ ሃሳብ እንዳላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለወጣቱ ያቀረቡት አማራጭ ሃሳብ ላይ ከፓርቲ ተወካዮችና ከከተማዋ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

በውይይቱ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢመረጡ የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ለመፍታት ያላቸውን አማራጭ ሃሳብና ፖሊሲ ለወጣቶቹ ገለጻ አድርገዋል።

ፓርቲዎች  በተለይም ስራ አጥነት፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች የኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ዋነኛ ችግር የሆኑትን ለመፍታት የያዙትን እቅድ አብራርተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርዎችና ሲቪል ተቋማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴና የአዲስ ትውል ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታምራት ማጬ ፓርቲያቸው ቢመረጥ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የያዙትን እቅድ ገልጸዋል።  የእናት ፓርቲ  የፖሊሲ ቡድን አባል ዶክተር አለማየሁ ወልደየስና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ(ኢዜማ)ተወካይ አቶ ይመስገን መሳፍንት በበኩላቸው ወጣቶችን በፖለቲካው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ያላቸውን አመራጭ አስረድተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች ፓርቲዎች ያቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ከቀናት በኋላ ለሚካሄደው የድምጽ መስጫ ቀን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ለማድረግ እንደሚረዳቸው አንስተው እንዲብራራላቸው ያሉዋቸውን ሃሳቦች ጠይቀዋል።ወጣቶች ያቀረቧቸውን ሃሳቦች እንደግብአት በመውሰድ በምርጫው ካሸነፉ የወጣቱን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ እንደሚሰሩ ፓርቲዎች አረጋግጠዋል።

ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ችግሮቻቸውን ይፈታል ብለው ላመኑበት ፓርቲ ድምጽ በመስጠትና በማስተባበር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ አንስቶ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጾ፤ ለድምጽ መስጫ ቀን ከሰባት ሺህ በላይ ወጣቶችን በታዛቢ፣ አስተባባሪና በአስተማሪነት ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ያቀረቡትን አማራጭ ሃሳብ እያስተዋወቁ ሲሆን ለድምጽ መስጫ አራት ቀን እስኪቀር ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።

የ2013 ስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ በጸጥታና በድምጽ መስጫ ህትመት ክፍተት ምክንያት ሰኔ 14 እና ጳጉሜ 1 ቀን በሁለት ዙር እንደሚካሄድ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም