አቶ ደስታ ሌዳሞ በ40 ሚሊዮን ብር የተገነቡ አገልግሎት መስጫዎችን መርቀው ስራ አስጀመሩ

48

ሀዋሳ ሰኔ 04/2013 ( ኢዜአ) -የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በጎርቼ ወረዳ በ 40 ሚሊዮን ብር ግንባታቸው የተጠናቀቀ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በክልሉ ጎርቼ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት በ40 ሚሊዮን ብር ግንባታቸው የተጠናቀቀ አገልግሎት መስጫዎችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ ነው፡፡

ሲዳማ ክልል ከሆነ ወዲህ በርካታ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ጥቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በወረዳው የተጠናቀቁ ተቋማትን  ከማስመረቅ ባለፈ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉት ባጠረ ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ተገቢው ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የነዋሪውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት በመሰራቱ በርካታ አካባቢዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የንፁህ መጠጥ ውሀ ተደራሽነትን ለማሳደግና የሀብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጎርቼ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፃዲቁ ባጢሶ በወረዳው 40 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በብልሽት ምክንያት ለስድስት ዓመታት አገልግሎ ሳይሰጥ የቆየውን የኬኔራ የንፁህ መጠጥ ውሀ ተቋም ዳግም ወደ ሥራ በማስገባት ከ40 ሺህ በላይ የሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

እንዲሁም የሀሮ ሺፋ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ፣ 19 ሚሊዮን ብር  ወጪ የተደረገበት የአስተዳደር ህንፃና ዘመናዊ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ከተመረቁት ውስጥ  እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የሀሮ ሺፋ ከተማ ነዋሪ አቶ ተሰማ ፉና እንዳሉት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የከተማው ነዋሪዎች የቆየ ጥያቄ ነው።

"በኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመኖር ምክንያት ብዙ ሥራዎች መስራት እየቻልን ሳንሰራ ቆይተናል" ያሉት አቶ ተሰማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥያቄያቸው ተመልሶ አገልግሎቱን  በማግኘታቸው እጅግ መደሰታቸውን ገልፀዋል ፡፡

ወጣት ፍሬው አለማየሁ በበኩሉ የአካባቢው ማህበረሰብ ረጅም ርቀት በመጓዝ የሚያገኘውን ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሀ ለመጠጣት ሲገደድ መቆየቱን ገልጿል።

አሁን ላይ የክልሉ መንግስትና የወረዳ አስተዳደር ጥያቄያቸውን ስለመለሱላቸው ደስተኛ መሆኑን ገልጻል።

"ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የአመራር አካላት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየወሰዱ ባሉት ቁርጠኛ አቋም የተሻሉ ነገሮችን እያየን ነው" ብሏል ፡፡

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎች አመራር አካላት ተገኝተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም