ከሁለትዮሽ ግንኙነት መርህ ያፈነገጠ እርምጃ - ኢዜአ አማርኛ
ከሁለትዮሽ ግንኙነት መርህ ያፈነገጠ እርምጃ
በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)
ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚመሰርቱት በትብብር ብንሰራ ምን አይነት የረጅምና የአጭር ጊዜ ጥቅም ማግኘት ወይም ማስከበር እችላለሁ በሚል ስሌት መነሻነት እንደሆነ የዘርፉ ብያኔ ያመለክታል። የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከመሰረቱት ሀገራት መካከል አንዱ ማግኘት የሚፈልገውን ጥቅም ካላገኘ ወይም በጥቅም ማስከበር ላይ አለመግባባት ከተፈጠረ በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ግንኙነቱን ሊያቋርጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት ነው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም የሚባለው።
ሀገራት ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን የሚመሩበት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን የሚቀርጹትም ይህን ስሌት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህ ውስጥ ሰጥቶ የመቀበል መርህ ቁልፍ ሚና አለው። ለዚህም ነው የዘርፉ ምሁራን ያለሰጥቶ መቀበል ዓለም አቀፍ ግንኙነት እውን አይሆንም የሚሉት፡፡
ሀገራት ጥቅማችን አልተከበረም፣ የኛን ጥቅም የሚጻረር ተግባር ተፈጽሟል ብለው ሲያስቡ ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ ቀደም ሲል ይከተሉት የነበረውን ፖሊሲ መለስ ብለው እንዲከልሱ አንዳንዴም የዲፕሎማሲ መርህን በመጣስ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የበላይነት ተጠቅመው የተለያዩ ጫናዎችን በማሳረፍ የሌላኛውን ሀገር እጅ ለመጠምዘዝ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ለዚህም በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ፣ ለአንድ ወገን ያደላና ሀሰተኛ የመገናኛ ብዙሀን ዘገባዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የፖሊሲ አውጭዎች የአንድን ወገን መረጃ በግብአትነት ይጠቀማሉ።
ለዚህም በቅርቡ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የባለስልጣናት የጉዞ ዕገዳ እና ዕገዳው የተጣለበትን ምክንያት ፊንላንዳዊው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሞ ፔካ ፓርቪያነን “Tigray Conflict: Homework Not Done by Western Countries Has Led to Wrong Policy Action” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ሀተታ ላይ ሲያብራሩ በትግራይ ክልል የተከናወነውን የህግ ማስከበር እርምጃ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ መረጃ ላይ ሳይመሰረቱ በሰሩት የተሳሳተ ዘገባ ምክንያት አሜሪካ የተሳሳተ ውሳኔ እንድትወስን ምክንያት መሆናቸውን አስፍረዋል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈችውን የቪዛ እገዳ አስመልከተው "የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈውን የቪዛ እገዳዎችን እቃወማለሁ'' በማለት በሴኔቱ ፊት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን መንግሥት ከሽብርተኛው ድርጅት ሕውሓት ጋር በተመሳሳይ ረድፍ ለማስቀመጥ መሞከር ተቀባይነት እንደሌለው፤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ሠላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየሰራች መሆኗን፤ ሰላምንና አንድነትን ከማምጣት ውጪ ሌላ አካሄድ እንዳልተከተልች በዚህም ውሳኔው ትክክል እንዳልሆነና እንደሚቃወሙት ጭምር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ሴናተሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም በቂ ግንዛቤ መጨበጥ አለመቻላቸውንና ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸው የአሜሪካ አካሄድ የጋራ ጥቅም አስጠብቆ ከመሄድ ይልቅ የራሷን ጥቅም ብቻ ለማስከበር የተከተለችው የተሳሳተ መስመር እንደሆነ አመላካች ነው።
ዲፕሎማሲ ወይም የሁለትና ከዛ በላይ ሀገራት የሁለትዮሽ ወይም ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ሀገራቱ ባላቸው የጋራ ጥቅም መርህ ላይ ተመስርቶ የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር “አሁን አሜሪካ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ቅድመ-ሁኔታ በማስቀመጥ የምልሽን የማታደርጊ ከሆነ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷ በሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ መግባት ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን” የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በቅርቡ ገልጸዋል።
በአንድ በኩል የመንግሥትን የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅም የሚያዳክም ተግባር እያከናወኑ በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ያለውን ችግር እንዲፈታ መጠየቅ የሚቃረኑ ጉዳዮች መሆናቸውን ይናገራሉ። መንግሥት ችግሩን እንዲፈታ ድጋፍ ማድረግ ሲገባ አቅሙ እንዲዳከም ማድረግ ግን ከበስተጀርባው ማሳካት የሚፈልጉት ሌላ ፍላጎት እንዳለ ለመረዳት ዕድል ይሰጣል ይላሉ።
አሁን አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ እንዲሁም የአሜሪካን ጥቅም ሊያስከብር የማይችል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ግርማ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የአጋርነት ግንኙነት ዶላር በመላክ እና ህይወት በመገበር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ፍጹም ተገቢነት እንደሌለው ይገልጻሉ። ለማሳያም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለውን ሽብርተኝነት ለመከላከል ክቡሩን የሰው ህይወት ለመገበር ሠራዊት ስታሰማራ አሜሪካ የሰው ህይወት የማይገዛ ዶላር ስትልክ መቆየቷን ያነሳሉ።
የህብር ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በአርትስ አብይ ጉዳይ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ አሜሪካ ኢትዮጵያ በመዳከሟ ጥቅሟን ታጣ ይሆናል እንጂ የምታገኘው ነገር የለም በማለት በመግለጽ፤ ለማሳያነትም ቀደም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለው የተረጋጋ መንግሥት፣ ጠንካራ ወታደራዊ አቅምና የኃይማኖቶች በጋራ የመኖር እሴት በአካባቢው ሀገራት ላይ ይስተዋል የነበረውን የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ለማስታገስ እድል ፈጥሯል፤ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር እንደነበረች በመግለጽ ኢትዮጵያ ባትረጋጋ ተጎጂዋ ራሷ አሜሪካ እንደምትሆን ይገልጻሉ።
አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ውዝግብ በአንዳች አስገዳጅ ስምምነት እንዲቋጭ ግፊት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል። አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር ይህ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ጫና ለማሳደር ከምትጠቀምባቸው ምክንያቶች መካከል በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ተጠቃሽ ነው። ሁኔታው እንደሚያሳስባት በመግለጽ ችግሩ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው በማሳሰብ፣ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረስና ከሽብርተኛው ቡድን ጋር ድርድር እንዲደረግ በመወትወትና ግፊት በማድረግ፣ እንዲሁም የሀገሪቱን ተቋማት ገለልተኝነትና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በቀጥታ የሚጋፋ ጥያቄ በማቅረብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረች መሆኑን ይገለጻል፡፡
እነኝህ አስተያየት ሰጪዎች አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል የኢትዮጵያን ጥቅም እየረገጠች መሆኑን ለማሳየት በቅርቡ እስራኤል በፍልስጤም ላይ የፈጸመችውን ጥቃት እና የደረሰውን ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ጉዳት በተመለከተ ባወጣችው መግለጫ እስራኤል ራሷን ለመከላከል ስትል የወሰደችው እርምጃ መሆኑን ገልጻ ተገቢነቱንም መመስከሯን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በሀገር መከላከያ ሠራዊቷ ላይ ጥቃት የፈጸመ ቡድን ላይ የወሰደችውን ሉዓላዊነትን የማስከበር እርምጃ ስህተት እንደሆነ በመግለጽ ጭራሽ ተደራደሩ የሚል ስላቅ የሚመስል መግለጫ ማውጣቷን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
“How to Wreck a Black Nation In the Age of “Black Lives Matter” በሚል ርዕስ የታተመ አንድ ጽሁፍ ላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው የጉዞ ክልከላ እና ሌሎች ማዕቀቦች በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመረኮዘ እንደሆነ አትቷል፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ለሦስት አስርት ዓመታት በርካታ ወንጀሎችን ሲፈጽም የነበረው ቡድን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ባለመቀበል እና በርካታ የጥፋት መንገዶችን ሲከተል ቆይቶ በመጨረሻ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ቀደም ሲል ወደ ነበረበት ሽምቅ ውጊያ ስልት መግባቱን አትቷል። ይህ አገር ላይ ክህደት የፈጸመ ቡድን ቀደም ሲል በተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ የሰገሰጋቸውን አባላቱን በተለይ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን እንዲሁም በዘረፈው ዶላር የገዛቸውን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን፣ አንቂዎች፣ ፖለቲከኞች እንደ ፕሮፓጋንዳ ማሽንነት በመጠቀም ላይ መሆኑን ጽሁፉ አስነብቧል።
በተጨማሪም ለ27 ዓመታት አግዝፈው ሲመለከቱት የነበረው የህወሃት አሸባሪ ቡድን በተወሰደበት እርምጃ ድምጹ መጥፋቱን ተከትሎ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሲ ኤን ኤን፣ ሮይተርስ፣ ኤፒ፣ ቢቢሲ እና ሌሎች ምዕራባውያን ብዙሃን መገናኛዎች ድርጅቱ ሲፈጽማቸው የነበሩትን ወንጀሎች ሁሉ በመደበቅ አጋርነታቸውን በግልጽ እንዳሳዩ በሀተታቸው ላይ አስነብበዋል።
አሜሪካ ለጣለችው እገዳ የእነዚህ አካላት የተሳሳተ መረጃ መስጠት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች መሥራት የሚገባቸውን የቤት ሥራ በአግባቡ ባለመስራታቸው ጭምር እንደሆነ ይነገራል። ይህ ለ27 ዓመታት የተተገበረው የተበላሸ አሰራር ውጤት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ኬይረዲን ተዘራ እና ዶክተር ካሳ ተሻገር ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መበላሸት የጀመረው ከ30 ዓመታት በፊት መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ኬይረዲን እና ዶክተር ካሳ ይህንንም ያመጣው መንግሥት በአምባሳደር ሹመት አሰጣጥ ላይ ሲከተለው የነበረው የተበላሸ አሰራር ነው ይላሉ። ይህ ለበርካታ ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የተበላሸ አሰራር ለመቀየር ታስቦ የተጀመረው የዘርፉ የሪፎርም ሥራ በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግና ሙሉ በሙሉ በባለሙያ እንዲሰራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ።
አሜሪካ እገዳውን ያሳለፍኩት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ጉዳይ እንድታስተካክል የሰጠኋትን የማስተካከያ ምክረ-ሃሳቦች ባለመቀበሏ ነው ትበል እንጂ በዋናነት ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ጉዳዩን ባልተገባ እና ትክክለኛ መረጃ ላይ ባልተመሰረተ ዘገባ አየሩን በመቆጣጠራቸው፤ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን በተለይም የህዳሴውን ግድብ መስዋዕት ለማድረግ በመፈለጓ መሆኑን፤ ይህም አሁን የተጀመረ ሳይሆን በዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የተጀመረ እንደሆነ ምሁራኑ ይገልጻሉ። የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ ስምምነት በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በግድ እንድትፈርም ለማድረግ በተለያየ መልኩ ለማግባባትና ጫና ለመፍጠር ከሞመከራቸው ባሻገር ስምምነቱን የማትፈርም ከሆነ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች“ አስከማለት የደረሰ አይን ያወጣ አድሎአዊነት የተሞላበት እንዲሁም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር መልዕክት ማስተላለፋቸውን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
ለዚህም ነው ምሁራኑ ኢትዮጵያ እውነታውን የሚያሳይ ዘገባ መስራት የሚችሉ መገናኛ ብዙሀን መገንባት፣ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ አምባሳደሮች እና አማካሪዎችን አፍርታ ቢሆን አሜሪካ የወሰደችው እርምጃ ቀጣናውን እልፍ ሲልም የአውሮፓ ሀገራትንና ራሷን አሜሪካንን ጭምር የሚጎዳ መሆኑን ባስረዱላት ነበር የሚሉት። ምክንያቱም አሜሪካ የጣለችው እገዳ የሚጎዳው አንድ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በውስጧ ያስጠለለቻቸውን የ26 ሀገራት ስደተኛ ዜጎችን ጭምር መሆኑን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ቢፈጠር እነዚህን ስደተኞች ጨምሮ ከ120 ሚሊየን በላይ ስደተኞች የሚያጨናንቁት የአውሮፓ ሀገራትንና ራሷ አሜሪካን መሆኑን በውል እንድትረዳ ማድረግ ይቻል ነበር ይላሉ።
አሜሪካ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርታ ለወሰነችው የተሳሳተ ውሳኔ በተሳሳተ መንገድ ሄዶ ምላሽ መስጠት ኢትዮጵያን ተጨማሪ ስህተት ላይ እንደሚጥላት፤ ያልተፈለገ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል የገለጹት ምሁራኑ ይህ ስህተት የመጣውም የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህን መሠረት ያደረገ ልምድና አረዳድ አናሳ በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ።
መንግሥት ይህን ችግር በመረዳት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሻክር ፍላጎት እንደሌለው እና ችግሩን ለመፍታት ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ማሳወቁ ስክነት እና ስሌት ላይ የተመሠረተ አካሄድ እንደሆነ ምሁራኑ ይስማሙበታል።
ይህ የተሳሳተ አካሄድ ኢትዮጵያን ወክለው በመላ ዓለም ያሉ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በየሀገሩ የሚገኙ ለሀገራቸው ቀናኢ የሆኑ ዜጎችን ማደራጀትና ማስተባበር ባለመቻላቸው፤ የኢትዮጵያን እውነት መረጃ ላይ በመመስረት ተንትኖ ለዓለም ማህበረሰብ ተደራሽ የሚያደርግ ጠንካራ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ባለመገንባቱ እና የዘርፉ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠባቸው እንደሆነ ምሁራኑ ያነሳሉ።
መሰል ችግሮች እንዳይገጥሙ ቢገጥም እንኳን በፍጥነት ማስተካከል እንዲቻል ሀገሪቱን ወክለው በመላ ዓለም የሚገኙ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን አቅም ማጎልበት፤ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ መሠረታዊ ማስተካከያዎችን ማድረግ፤ በየአካባቢያቸው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብና ማደራጀት እንዲሁም ለሀገራቸው በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማበረታታት፤ ሀገሪቱን ከሚመሩ የመንግስት ሀላፊዎች አንደበት የሚነገሩ ንግግሮች የተመረጡ፣ የተመጠኑና የተጠኑ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ምሁራኑ ይመክራሉ፡፡
በተጨማሪም ሀገር ለውጭ ጣልቃ ገብነት የምትጋለጠው የውስጥ አንድነቷ ተናግቷል ወይም ችግር ገጥሞታል ተብሎ ሲታመን በመሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ጥቅምና በሀገር ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ልዩነት ካለም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መወያየት፣ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው አካላት ልዩነታቸውን መነሻ በማድረግ የሚወራወሯቸውን ቃላት መምረጥና ከተቻለ የውስጥ ጉዳያቸውን በውስጥ የሚጨርሱበት አሰራር ቢዘረጉ፤ ምሁራን ሀገር እንዲህ ባለው ችግር ላይ ስትወድቅ ዝምታቸውን ሰብረው የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት የሚችሉበት ጠንካራ አደረጃጀትና አሰራር መዘርጋት ተመሳሳይ ችግሮችን ለመመከት እንደሚያስችል ይገልጻሉ።