የመከላከያ ስፖርት ክለብ ነባር ስሙን ለመመለስ የሚያስችል ሲምፖዚየም አካሄደ

70

ሰኔ 03/2013 (ኢዜአ) የመከላከያ ስፖርት ክለብ ወደቀደመ አቋሙ ለመመለስ የሚያስችለው ሲምፖዚየም አካሄደ።
የክለቡ ድክመቶችን ማረም ወደ ነበረበት አቋም በሚመለስበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ሲምፖዚየም ዛሬ ተካሂዷል።

የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ከምልመላ እስከ ስልጠናና ውድድር ክለቡን ሊያጠናክርና ተተኪ እንዲያፈራ ለማድረግ ያስችላል ብለው ያመኑበትን ሀሳብ አቅርበዋል።

በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪና ስመጥር እንዲሆን መሰራት እንዳለበትም ነው ምክራቸውን የለገሱት።

የክለቡ ዳይሬክተር ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ እንደተናገሩት ክለቡ በአሁኑ ወቅት ነባር ስምና ክብሩን ለማስጠበቅ በሚያስችለው አቋም ላይ አይደለም።

ተተኪና ውጤታማ ስፖርተኞች ለማፍራት ትኩረት አለመስጠቱ ለዚህ ችግር እንደዳረገው ነው የገለጹት።

ክለቡ በሚወዳደርባቸው በአትሌቲክስና በእግር ኳስ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ሲምፖዚየሙ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍሥሐ ወልደሰንበት በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ ክለቡ በቀጣይ  ስኬታማ የሚያደርጉ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩና ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ክለቡ በአገሪቱ ስፖርት ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኖ ለመቀጠል፣ ማህበራዊ መሰረቱን ለማስፋት፣ ጉድለቶችን ለመፈተሽና ስኬቱን ለማስቀጠል ይረዳዋል ነው ያሉት።

ባለድርሻ አካላት በሚሰጧቸው ግብዓቶች ላይ በመመስረት ጠንካራ ክለብ ለማውጣት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንዓ ያደታና የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ተገኝተዋል።

ዶክተር ቀንዓ ከተሳታፊዎች የተገኙ ሀሳቦችን በግብዓትነት በመጠቀም ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የመከላከያ ስፖርት ክለብ 'ጠቅል' ተብሎ ከተመሰረተበት ከ1937 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ አሻራውን ያሳረፈ ክለብ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም