የኢትዮ-አውሮፓ ሕብርት የጋራ ምክክር ተካሄደ

105

ሰኔ 3 / 2013 (ኢዜአ) በኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የጋራ ምክክር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም በጋራ መሪነት ተካሂዷል ።

ምክክሩ በኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የትብብር ጉዳዮች፣ የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ እንዲሁም በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ በማተኮር የተካሄደ ተነግሯል።

በወቅቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል የሚደረገው ቋሚ ምክክር በኮቶኖ ስምምነት እንዲሁም በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል እ.ኤአ በ2016 የተፈረመውን የስትራቴጂያዊ የትብብር ሰነድ መሰረት ያደረገ ሰለመሆኑ ገልጸዋል።

በወቅቱም ተሳታፊ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮች በሰጡት አስተያየት የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵየ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት በተያዩ መልኩ ድጋፍ ማደረጉን አስታውሰው፣ ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርስባትን ተጽዕኖ ለመከላከል የተከተለችውን መንገድ እንደሚያደንቁ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን ለመክፈት በተሌኮም ሴክተር የታየው ተግባራዊ እርምጃ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል አውሮፓ ኩባንያዎች ከረጅም ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ በወጪ ንግድ እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ አስተዋጸኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ በሚወጡ ህጎች በአፈጻጸም ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ አስቀድሞ ምክክር እንዲደረግ ያላቸውን አስተያየት ገልጸዋል።

የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ቅንጅታዊ አሰራሮች የበለጠ ለማሻሻል የሚቻልባቸው መንገዶች እንዲታዩ፣ በክልሉ የግብርና ተግባራት ትኩረት የሚሹ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረትን የሚደግፉ መሆኑን፤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ተቋም መካከል ገለልተኛ የጋራ ምርምራ ለማድረግ የተጀመረው ሂደት አንደሚያደንቁ ገልጸዋል።

በስደተኞች ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እንዲሁም መንግስት ለፕሬስ ነጻነት ተገቢው ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም መደረጉን እንደሚያደንቁ ገልጸው፣ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ከሎጀስቲክ ስርጭት አንጻር የሚያጋጥሙ ችግሮች ትኩረት መሰጠት ያለበት መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው ምንም አንኳ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የደቀነው አሉታዊ ተጽእኖ ቢኖርም ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በመፍጠሯ የውጭ ቀጥታ አንቨስትመንት ፍሰት ከመሳብ አንጻር አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን አንስተዋል።

አያይዘውም ኢንቨስተሮች የሚያጋጥማቸውን ማነቆዎች ለመፍታት አገራዊ የቅንጅት መድረክ መቋቋሙን አንስተው፣ የአውሮፓ ህብረት አገራት ኩባንያዎችም የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ለመከላከል ከአውሮፓ ህብረት ለተደረገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

አያይዘው በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የተሟላ መሰረት ልማት ያለው የቅሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ መዘጋጅቱን ጠቅሰው፣ በዘርፉ በመሰራት አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ከማሳደግ አንጻር ተሳትፎ አንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ለሚሰማሩ አካላት ያልተገደበ ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን አስታውሰው፣ ለእርዳታ አቅራቢ ሰራተኞች ደህንነት ሲባል በተወሰኑ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ነግር ግን በአጠቃላይ በክልሉ የተደራሽነት ችግር መኖሩን አመላካች አለመሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በሁለተኛውና በሶስተኛው ዙር 5.2 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው ፤የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊዎችን በተመለከተ የሚቀርበው አሀዝ ቀደም ሲል በክልሉ ያሉና የተለየ ሀብት የተመደበላቸውን ተፈናቃዮች፣ የምግብ ዋስትና ተረጂዎች እንዲሁም ስደኞችን ቁጥርን ከግምት ያላስገባና የተጋነነ መሆኑን አንስተዋል።

አክለውም በሲቪል እና ወታደራዊ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ ለማሳደግ የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ደመቀ አንስተዋል።

በክልሉ የግብርና ስራዎች የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ የግብርና ግብዓቶች የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እየወጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሂደቱን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በትግራይም የተፈናቀሉ ዜጎች ከዝናብ ወቅት በፊት ለመመለስ እንዲቻል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የሕወሓት ቅሪቶች በክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር አባላት እና ሌሎች ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ ማድረግ መቀጠላቸውን ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታውን በሚዛን በማየት መሰል ተግባራትን በይፋ መኮንን እንደሚገባው አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ወደ ሌላ በማዛወር አስፈላጊው ግብዓት በሟሟላት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን እንዲሁም ተጨማሪ መጠለያዎችን የማቋቋም ስራዎች ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሸን ጋር በመተባበር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ የፌደራል ፖሊስ ከሚሽን ከትግራይ ክልል ጊዚዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር አስፈላጊው ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በተያያዘም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ተቋም ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የጋራ ምርመራ ለማካሄድ ባለሙያዎች በክልሉ ማሰማራታቸውን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ ህብረትም በተመሳሳይ ስራውን እንዲጀመር መንግስት እየጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ግጭት በነበራቸው በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታዎች በመሻሻላቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ የሚያስችል ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተም መንግስት ከመቸውም ጊዜ በላይ የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ማድረጉን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ባፈነገጠ መልኩ የተለየ ተልዕኮ በመያዝ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ጋዜጠኞች ስለመኖራቸው አንስተዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከናወን መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ አንዲደራጅ መደጉን ገልጸዋል።

የሎጀስቲክ ስርጭት ችግሮችን ለመቅረፍም ቦርዱ የጊዜ ሰሌዳው በመከለስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት ማድረጉን አንስተዋል። አክለው በአሁኑ ወቅት ወደ 40 ሚዮን የሚጠጋ መራጭ መመዝገቡን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በመድረኩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገው ጥልቅ ውይይት በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የስራቴጂያዊ ግንኙነት አመላካች መሆኑን ጠቅሰውዋል።

አቶ ደመቀ የአውሮፓ ህብረት የኢትየጵያ ቀዳሚ የስራቴጂክ አጋር መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይህም ኢትዮጵያ ከህብረቱ እንዲሁም ከአባል አገራቱ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላት ዘርፈ ብዙ ትብብር አመላካች መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንኙነቱን የበጠ አጠናክሮ መስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

መረጃው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም