በአዳማ ከተማ ጓደኛቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ የፈጸሙ 3 ግለሰቦች በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ ጓደኛቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ የፈጸሙ 3 ግለሰቦች በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጡ
አዳማ ግንቦት 30/2013(ኢዜአ) በአዳማ ከተማ በጓደኛቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግደያ ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱ ሶስት ግለሰቦች በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።
አሸናፊ ንጉሴ፣ ተመስገን ደስታና አስቻለው በቀለ የተባለት እነዚህ ግለሰቦች በአዳማ ከተማ ቦኩ ሸነን ቀበሌ ህዳር 26/2013ዓ.ም ሾፈር የነበረው ጓደኛቸውን ዱባለ አሰፋን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው በማስረጃ እንደተረጋገጠባቸው የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እንስፔክተሯ እንዳሉት፤ ግለሰቦቹ የጎንዴ ዱቄት ፋብሪካ ሾፌር የነበረው ጓደኛው ቤት ታደርሰናለህ በሚል ሁኔታውን በማመቻቸት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ በገመድ በማነቅና አንገቱ ላይ በስለት በመውጋት ከገደሉ በኋላ አስክሬኑን ገደል ውስጥ እንደከተቱ የክስ መዝገባቸው ያመለክታል።
ሟች የያዘውን የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3- 43350 አ.አ "ዶልፍን" ተሽከርካሪ ዘርፈው መሰወራቸውን በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች የተረጋገጠባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ግለሰቦቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸውና ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውን የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ኢንስፔክተር ወርቅነሽ አስታውቀዋል።