የዜጎችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- ዶክተር አለሙ ስሜ

ነገሌ፤ ግንቦት 30/2013 (ኢዜአ) የዜጎችን እኩልነትና ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ማዕከላት አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ፡፡
ዶክተር ዓለሙ፤ በጉጂ ዞን የተገነቡ  የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስት በጥፋት ሀይሎች ጫና ውስጥ  ሆኖ የጀመራቸውን የመሰረተ ልማት ተቋማት ሰርቶ በማጠናቀቅ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እያሳየ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ፣ የተጠናቀቁና ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑ ከ11 ሺህ በላይ መካከለኛና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወነውን  ስራና ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ በውስጥ የጥፋት ሀይሎች የሚደረግ ትንኮሳ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና የብልጽግና ጉዞን ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውንም ጫናና ተጽዕኖ አንቀበልም ሲሉ አስታውቀዋል።

በዚህም  የዜጎችን እኩልነትና ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ  ዶክተር አለሙ ስሜ ገልጸዋል። 

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በ880 ሚሊዮን ብር የተጀመሩ ፕሮጀክች የግንባታ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥ እስካሁን በዞኑ አዶላ ሬዴና አናሶራ ወረዳዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት የተዘጋጁ 108 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ጠቅሰዋል።

ከተጠናቀቁት መካከል የመንገድ፣ መጠጥ ውሀ፣ ትምህርት፣ ጤናና የመብራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዋና ዋናዎቹ  እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል እና ፌደራል  መንግስት ጋር በመተባበር ከህዝብ ሲነሱ ለነበሩ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለመሰረተ ልማት ጥያቀዎች ደረጃ በደረጃ እየተሰጠ ያለው ምላሽ የብልጽግና ጉዞን በተግባር የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ከአናሶራ ወረዳ ይርባ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ነጌሳ ቦርሴ  በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢያቸው መንግስት የሰራላቸው የውስጥ ለውስጥ መንገድና ድልድይ የነበረባቸውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲመጣ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው በአቅራቢያቸው የተገነባው የቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ልጆቻቸው በሙያ ሰልጥነው ስራ በመፍጠር እራሳቸውን ለመቻል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

ፍትሀዊ የልማት  ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት የጀመረው ጥረትና ተነሳሽነት ለቀሩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

በጉጂ ዞን  አዶላ ሬዴና አናሶራ ወረዳዎች  በመዘዋወር በተካሄደው የልማት ፕሮጀክቶች የምረቃ ስነ-ስርዓት የፌደራል፣ ክልል ፣ ዞንና ወረዳ  የመንግሰት ስራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም