በ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተገነባው የዘይት ፋብሪካው የስራ እድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ከፍተኛ ሚና እንደሚወጣ ተገለጸ

134

ባህርዳር፣ ግንቦት 29/2013 (ኢዜአ) በደብረማርቆስ ከተማ በ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተገነባው " ደብሊው ኤ" ዘይት ፋብሪካ የአርሶ አደሩን ምርት ተቀብሎ በማቀነባበር፣ የስራ እደል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ከፍተኛ ሚና ይወጣል ሲሉ የፋብሪካው ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው አስታወቁ።

ፋብሪካው የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነገ ይመረቃል።

ባለሀብቱ ዛሬ ለኢዜአ በሰጡት መገለጫ እንዳሉት ፋብሪካው በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የዘይት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት የተቋቋመ ነው ።

ፋብሪካው በቀን 18 ሺህ ኩንታል፤ በአመት ደግሞ እሰከ 6 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል በግብአትነት እንደሚጠቀም ገልጸዋል።

በቀን 1 ሚሊዮን 350 ሺህ ሊትር ዘይት በማምረት ወደ ገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

ዘይት ፋብሪካው አርሶ አደሩ የቅባት እህል በስፋት እንዲያመርት በማድረግ የምርት አቅርቦት ትስስር እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ ለ1ሺህ 500 ሰዎች የስራ እደል መፍጠሩን ጠቅሰው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከ3 ሺህ የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

በሀገር ውስጥ ማምረት ባለመቻሉ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገነባውን ዘይት እስከ 60 በመቶ የማስቀረት አቅም እንዳለው አብራርተዋል።

የሀገሪቱን የምግብ ዘይት አቅርቦት ለመፍታት ሌሎች እስከ ስምንት የሚደርሱ ፋብሪካዎች እንደሚያስፈልጉ የገለጹት አቶ ወርቁ "ለተግባራዊነቱ ሁሉም ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

ፋብሪካው የመብራት ውሀና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት በመሆኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርቱን ለተጠቃሚ እንደሚያቀርብ አመላክተዋል።

ፋብሪካው ለስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረትና የአርሶ አደሩን የቅባት እህል ተቀብሎ በማቀነባበር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በ11 ሄክታር ላይ ያረፈው "ደብሊው ኤ" የዘይት ፋብሪካ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነገ እንደሚመረቅ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም