የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 11 ቀናት ብቻ ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ መንዝሯል

166
አዲስ አበባ ሀምሌ  27/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት አስራ አንድ ቀናት ብቻ ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማካሄዱን ገለጸ። በተመሳሳይ የአዋሽ ባንክ ባለፉት አስራ አራት ቀናት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማካሄዱን አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግለሰቦች የያዙትን የውጭ ሀገር ገንዘብ በባንክ እንዲመነዝሩ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ በባንክ እየተካሄዱ ያሉ የውጭ አገራት መገበያያ ገንዘቦች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ የኮርፖሬት ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ሀብቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባንኩ ባለፉት አስራ አንድ ቀናት በአማካኝ በቀን ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር በላይ መንዝሯል። ከዚህ ቀደም በቀን በአማካይ ከ650 ሺህ ዶላር ያልበለጠው የውጭ ምንዛሬ በአሁኑ ወቅት ከስድስት እጥፍ በላይ ማደጉን ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል። በተመሳሳይ የአዋሽ ባንክ በበኩሉ የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አስታውቋል። ባለፉት አስራ አራት ቀናት ብቻ በተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መካሄዱን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም