ለሠላም ስንል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል - ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ

90

ግንቦት 25 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ለሠላም ስንል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል” ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የተቋቋመው የጸጥታ ግብረሃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ ገለጹ።

የጸጥታ ችግር ተከስቶበት በነበረው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በከሚሴ ከተማ ደዋ ጨፋ ወረዳ ተረፍ ቀበሌ አስተዳደር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያስተሳስር የሰላምንና አብሮነት ሥነሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የጸጥታ ግብረሃይሉ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ “መሠረታዊ ዕርቅ እና ሰላም እንዲፈጠር የሐይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና በጎ አሳቢ ግለሰቦች ከፍተኛ ሚና አላቸው” ብለዋል።

በዚህም ሰላምን ለማስፈን የሚካሄዱ ተግባራትን ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመቆም ማገዝና መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በመግለጽ አሁንም "ለሠላም ስንል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ሰላም ከሌለ ሁላችንም አብረን ለመኖር የማንችል በመሆኑ ለሠላም የሚያስፈልገውን ዋጋ በመክፈል ሁሉም ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

መጪው ምርጫና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን "ሠላምን በማስጠበቅ አገራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካት ህብረተሰቡ አንድነቱን መጠበቅ ይገባዋል" ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም