አቶ አገኘሁ ተሻገር በጎንደር ከተማና አካባቢው በ7 ቢሊዮን ብር ወጭ በግንባታ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እየጎበኙ ነው

964

ጎንደር፣ ግንቦት 25/2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በጎንደር ከተማና አካባቢው በ7 ቢሊዮን ብር ወጭ እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን እየጎበኙ ነው።

በርዕሰ መስተዳደሩ እየተጎበኙ ከሚገኙ የመሰረተ ልማቶች መካከል በ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጭ እየተገነባ የሚገኘው የመገጭ የመጠጥ ውሃና መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው።

በተጨማሪም በ860 ሚሊዮን ብር ወጭ እየተገነባ የሚገኘው ከአዘዞ መሰረት ትምህርት ቤት ያለው የ10 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት አስፓልት መንግድ ስራ በርዕሰ መስተዳደሩ ተጎብኝተዋል።

እንዲሁም በጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚሰጠው የአንገረብ ግድብን የደለል መሞላት ችግር ለማቃለል በ100 ሚሊዮን ብር ወጭ የተጀመረው የማጣሪያ ስራም የጉብኝቱ አካል ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የመገጭ መስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክትን በመጭው ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ በመንግሰት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

በጉብኝቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ የከተማው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የከተማው ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ርዕሰ መስተዳደሩ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ የቀጣይ አቅጣጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።