በቦረና ዞን ግንባታቸው የተጠናቀቀ 37 የመጠጥ ውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

64

ነገሌ ግንቦት 25/2013 (ኢዜአ ) በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተገነቡ 37 የመጠጥ ውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የቦረና ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የውሃ አቅርቦትና ክፍፍል አስተዳደር አቶ ከበደ ገብረማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የወሀ ተቋማት በጀኔነተር፣ በእጅ ፓምፕና በጸሐይ ሃይል የሚሰሩ ናቸው።

"በተጨሪማሪም በድርቅና በበጋ ወራት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ታሳቢ ተደርገው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነቡ ሁለት ጥልቅ የውሃ ባንኮችም ይገኙበታል" ብለዋል።

ተቋማቱ እያንዳንዳቸው እስከ 130 ሜትር የሚደርስ ጥልቀትና 600 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የውሀ ተቋማቱ ከመጋቢት 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየሰጡ ባለው አገልግሎት 250 ሺህ የአርብቶ አደር ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም  60 ሺህ የቤት እንስሳት ተጠቃሚ  መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የመጠጥ ውሃ ተቋማቱ ከፌደራልና ከክልሉ መንግስት እንዲሁም  ከኬር ኢትዮጵያ በተመደበ 87 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሆናቸን አብራርተዋል፡፡

መንግስትም የአካባቢውን የውሀ እጥረት በመረዳት በየዓመቱ በ40 ቦቴ ተሽከርካሪዎች ለገጠሩ ህዝብ የመጠጥ ውሃ እያከፋፈለ መሆኑን ጠቁመው የተገነቡት የውሀ ተቋማት ችግሩን ለማቃለል የላቀ አስተዋጻ እንዳላቸው አመልክተዋል።

በዞኑ ዲሎ ወረዳ የሀርበሌ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ቶኮ ውቃሃ  ከዚህ ቀደም በየቀኑ የሶስት ሰዓት የእግር መንገድ በመጓዝ ውሀ ሲቀዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።

"አሁን ያገኘነው እረፍት እርካታው ወደር የለውም፤ የአመታት ጥያቄያችንን በማዳመጥ ችግሩን ለማቃለል የመጠጥ ውሃ ለሰሩልን ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን" ብለዋል፡፡

 በአካባቢው የነበረው የመጠጥ ውሃ ችግር ማገዶ ለቅሞ ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከብት ከማሰማራትና ከመጠበቅ እንዲሁም  ልጆችን ከመንከባከብ በላይ የከፋ ጫና እንደነበረው ያስታወሱት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ዲማ ዶኮ ናቸው።

በተገነባላቸው የውሀ ተቀም የአመታት የመጠጥ ውሃ ጥያቄያቸው  ከመመለሱ ባለፈ ለሴቶች ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢያቸው ንጹህ ውሃ መገኘቱ የስራ ጫናን ከማቃለል ባለፈ  የጊዜ ብክነትና ድካምን በመቀነሱ እፎይታ እንደፈጠረላቸው በደስታ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም