የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፌን በኢትዮጵያ ውጤታማ ጉብኝት ነበራቸው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

61

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25 /2013 (ኢዜአ) የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፌን በኢትዮጵያ ውጤታማ ጉብኝት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው ዓበይት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ክንውኖችን አንስተዋል። 

ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያና አሜሪካ ጉዳይን በተመለከተ ሴናተር ኢንሆፌን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጀምሮ ከከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻከር እንዲባባስ እንደማትፈልግ ገልጸው፤ መንግስት በጋራ ወዳጆች አማካኝነት ግንኙነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

"በአንዳንድ ስሜታዊ በሆኑ ሰዎች የሚራመዱና የሚንፀባረቁ አስተያየቶች የግለሰቦች እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቋም እንዳልሆኑ እንዲታወቁ" ሲሉም ገልጸዋል። 

"ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ከማንኛውም አገር ጋር ጠንካራ ግንኙነትን ማጠናከር ነው የምትፈልገው፤ የወዳጅነት ወሰንም የለም" ሲሉም ተናግረዋል አምባሳደሩ።

በሳምንቱ 10 አገራት የአምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም በየአገራቱ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩንና ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ እንዳስረዷቸው ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ከሞሮኮ አቻቸው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩም ነው ያመለከቱት።

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ከዚህ በፊት የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ በጋራ መነጋገራቸውንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከተለያዩ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተግባራት ተከናውነዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት መካከል ውይይት መደረጉንም ጠቁመዋል። 

"ባሳለፍነው ሳምንት 1ሺህ 147 ዜጎች ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል" ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በኢትዮጵያ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎችም በውጭ አገራት ለአብነትም በኖርዌይ፣ ካናዳ እና ጣልያን መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም