ለወጣቱ ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም —የሸካ ዞን ነዋሪዎች

997

ሚዛን ሀምሌ 27/2010 በቴፒ ከተማ ከደኢህዴን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር እየተወያዩ ያሉት የሸካ ዞን ነዋሪዎች ወጣቱ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተገቢውን  ትኩረት እንዳልተሰጠው ገለጹ፡፡

በውይይቱ ወቅት በተለይም የቴፒ ከተማ ወጣቶች ያነሱት ጥያቄ ለወጣቱ ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም የሚል ነው፡፡

ወጣቶቹ የአካባቢው አመራሮች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ስላልተመቻቹላቸው ከአካባቢው ተሰደው እንዲኖሩ መገደዳቸውን ነው የተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግር እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል፡፡

መንግስት ህዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን አመራሮች አሰራር እንደማይፈትሽ ያመለከቱት ነዋሪዎቹ የአመራር ምደባም የትምህርት ዝግጅታቸውንና አቅማቸውን ያገናዘበ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሸካ ዞን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች እየተሰታፉበት ባለው የቴፒው ውይይት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የደኢህዴን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡