በትግራይ ክልል ለዘንድሮው መኸር ከ70 በመቶ በላይ መሬት ታርሷል

79

አዲስ አበባ፣  ግንቦት 21/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ለዘንድሮው መኸር እስካሁን ከ70 በመቶ በላይ መሬት መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘር አቅርቦት ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የመኸር እርሻ ከሌሎች ክልሎች እኩል እየተሰራና በጥሩ አፈጻጸም ላይ ይገኛል።

በክልሉ በነበረው ችግር የመስኖ አውታሮች፣ የሰርቶ ማሳያዎች፣ የወረዳና የቀበሌ የግብርና ማዕከሎች የምርምር ጣቢያዎችና ሌሎችም የግብርና መሳሪያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በክልሉ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ከነበረው ችግር ተቋማቸውን ለማትረፍ ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የህግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቆ ወደ መልሶ ግንባታና ሰብአዊ ድጋፍ ከተገባ በኋላ መልሶ የማቋቋም ስራውን የሚደግፍ በሚኒስትሮች የሚመራ ሀገራዊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

በክልሉ አርሶ አደሮች ወደ እርሻ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ግብረ ሃይሉ፣ የክልሉ ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በመቀናጀት የሰሩት ስራ ውጤታማ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች የመኸር እርሻን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በስልጠና የማገዝና የማብቃት ስራ የተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የክልሉ የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ አፈጻጸም አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ ሲሆን አርሶ አደሮችም ከችግር ለመውጣት የእርሻ ስራውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

በምርት ዘመኑ በክልሉ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ70 በመቶ በላይ መታረሱን ጠቁመዋል።

ለግብርና ሥራው ከሚያስፈልገው 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያም ከ59 በመቶ በላይ መቀሌ በሚገኘው መጋዘን ደርሶ ለአርሶ አደሮች በመከፋፈል ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ 120 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማዳረስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ችግሮች መጠነኛ እጥረት በማጋጠሙ ችግሩን ለመፍታት በሌሎች ክልሎች ካሉ የመጠባበቂያ የዘር ክምችት ተወስዶ እየተከፋፈለ መሆኑን አቶ ሳኒ ገልጸዋል።

ለመኸር እርሻ እንቅስቃሴው አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ሃብት የማስባሰብ ስራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥ 504 ሚሊዮን ብሩ ከተለያዩ አጋር አካላት በመሰብሰብ ለግብርናው ግብዓትማሟያ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ቀደም ሲል በየምርት ዘመኑ እስከ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም