ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የሆኑ 41 የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ነው

105

ጋምቤላ ፤ ግንቦት 20/2013 (ኢዜአ) ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከሰው ሀብት ልማት በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የሆኑ 41 የምርምር ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው ''ምርምርና ፈጠራ ለዘላቂ ልማት’’ በሚል መሪ ሀሳብ አራተኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በኮንፈረንሱ መድረክ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ እንዳሉት፤ ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለተካዊ እድገት ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር  ስራዎችን ዓይነተኛ ፋይዳ አላቸው።

ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ከሰው ሀብት ልማት በተጨማሪ ችግር ፊቺ ምርምር ስራዎችን በማከናወን ለሀገር እድገት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ከ2008ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የአካቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን  ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመታም 41 የምርምር ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው እየተካሄዱ ያሉት የምርምር ፕሮጀክቶች ግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ ማህበራዊ ሳይንስ፣ እንስሳት ሀብትና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።  

በምርምር ኮንፈረንሱ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የምርምርና ጥናት ሰራዎች ተጨማሪ ግብዓት የሚገኝበት ይሆናልም ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ በማህበራዊ፣ ተፈጥሯዊ ሳይንስና ሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ 16 ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው  ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።

በኮንፈረንሱ ከሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች የተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ከጋምቤላ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም