በኢሉአባቦር በመስኖ ከለማው መሬት ካለፈው ዓመት በ900 ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ

66
መቱ ግንቦት 7/2010 በኢሉአባቦር ዞን ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ900 ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡ የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ስራ አስከያጅ አቶ በዳሳ ነጋሳ እንዳሉት ዘንድሮ በ13 ወረዳዎች ከ47 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ35ሺ ሄክታር በላይ መሬት በሁለቱ ዙር መስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ በ19ሺ100 ሄክታር መሬት ላይ ከለማው የጓሮ አትክልት፣ ስራስርና የበቆሎ ሰብል ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የለማው መሬት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ ባይኖረውም ምርታማነቱ ግን በ900 ሺህ ኩንታል እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በተፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት አብዛኛው  ሰብል ላይ ጉዳት በመድረሱ  በመስኖ የተገኘውን  ምርት ዝቅ አድርጎት ነበር ፡፡ ዘንድሮ  ተስማሚ የአየር ንብረት በመኖሩ አርሶአደሩ ሙሉ አቅሙን በመጠቀም እንዲያለማ በተደረገው ጥረት የተሻለ ምርት እንዲገኝ ምክንያት መሆኑን አቶ በዳሳ አስረድተዋል ። በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ስራ በአብዛኛው በስራስር እና በቆሎ ሰብል የተሸፈነ ከ14ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት እየለማ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ከአንድ ሚሊዮን  ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ በቡሬ ወረዳ   የኦቦ ሚሪጋ ቀበሌ አርሶአደር ወንድሙ መኮንን በበኩላቸው ባላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት  ላይ የስራስር ሰብል በማልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም