በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

54
አዳማ ሀምሌ 26/2010 በየትምህርት ተቋማት አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ለመግታት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ። በተያዘው የበጀት ዓመት በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምረዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በሀገር ደረጃ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ባለፉት አስር  ዓመታት በበሽታው ህይወታቸው የሚልፈው  70 በመቶ እና አዲስ የመያዝ ምጣኔ ደግሞ በ90 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡ ሆኖም  በህብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው መዘናጋት የኤች አይቭ ኤድስ ስርጭት ዳግም እያገረሸ ነው። " በሀገራችን ከ600ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል" ያሉት አቶ ብርሃኑ በየዓመቱ ከ15ሺህ በላይ የሚሆኑ በሽታዎች ህይወታቸውን እንደሚያልፍም ጠቁመዋል። ሚኒስትር ዴኤታው እንዳመለከቱት መድረኩ የተዘጋጀት አምራቹን በተለይ ወጣቱ ኃይል  ከኤች አይቪ ኤድስ ተጋላጭነት ለመታደግ  በትምህርት ተቋማት የተፈጠረውን መዘናጋት ለማንቃት ነው። በበሽታው ስርጭት ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት ያለበትን የህብረተሰብ ክፍል እውቀት፣ክህሎትና አቅም በመገንባት የባህሪይ ለውጥ እንዲመጣ የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የትምህርት ሚንስቴር ዴኤታ አቶ ተሾመ ለማ በበኩላቸው "በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስፋፋ የመጣውን  የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ለመግታት መስሪያ ቤታቸው ስትራቴጅክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል" ብለዋል። በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ለበሽታው  አጋላጭ የሆኑ ባህሪያት በተለይም  የጫት፣መጠጥና ሽሻ ቤቶች፣የምሽት  ጭፈራ ቤቶችና ተያያዥ ችግሮችን በማስወገድ አካባቢውን የማጥራት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ ሀገራዊ ንቅናቄ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰው በተያዘው የበጀት ዓመት በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አስረድተዋል። በንቅናቄው የህይወት ክህሎት፣የአቻ ለአቻ፣የስነ ተወልዶ ጤና፣የምክክርና ድጋፍ አገልግሎቶችን ያካተተ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አቶ ተሾመ አመልክተዋል፡፡ የፌዴራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሻሎ ዳባ በመድረኩ ባቀረቡት ጽህፍ  ከ15 እስከ 24 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ወጣቱና አምራቹ ኃይል ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለበሽታው  ተጋላጭነቱ እጀግ ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የወጣቱን ትውልድ ህይወት መታደግና የባህር ለውጥ እንዲመጣ መስራት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀና በሚቆየው የምክክር መድረክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣የሰቪክ ማህበራትና በጤና ዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም