ቻይና ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች

79

ግንቦት 17/2013 (ኢዜአ) ቻይና ለትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከልና ለሌሎች የህክምና አገልግሎት የሚውል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ ካውንስለር ሊ ዩ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ አስረክበዋል።

ድጋፉ ሰባት የመተንፈሻ እገዛ የሚሰጡ መሳሪያዎች (ቬንትሌተሮች)፣ 36 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) እንዲሁም 1 ሺህ 500 የህክምና አልባሳትን አካትቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የህክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ኤምባሲው ገልጿል።

ድጋፉ የትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝና ለመደገፍ እንደሚውል ተጠቁሟል።   

በኤምባሲው የኢኮኖሚና የንግድ ካውንስለር ሊ ዩ አንደተናገሩት፤ ድጋፉ ከቻይና መንግሥትና ከቻይና ኩባንያዎች የተሰባሰበ ነው።

ጎን ለጎንም ካውንስለሯ የሥራ ጊዜያቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመው ወደ አገራቸው ሲመለሱም የአገራቱ ግንኙነት እንዲጠናከር እሰራለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1970 ነበር።  

ሁለቱ አገራት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ የልማትና የኢኮኖሚ ትብብር በመፈራረም እየሰሩ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም