አሜሪካና ኢትዮጵያ ከነበራቸው ግንኙነት አንጻር ማእቀብ የመጣል ውሳኔ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው

105

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማእቀብ ቻይና እና አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የበላይነትን ለመያዝ የሚያደርጉት ትንቅንቅ ማሳያ ነው ሲሉ እንግሊዛዊው የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኝ ቶም ፎዲ አመለከቱ።

 ተንታኙ ቻይና ፣ሰሜን ኮሪያ ፣እንግሊዝ ፣አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን በተመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ላይ ትንታኔዎችን የሚሰጡ ሲሆን ለአር ቲ፣ ለሲጂቲኤን፣ ለቻይና ዴይሊ፣ ለግሎባል ታይምስ፣ ለክሮኒክልና ለሌሎች አለምአቀፍ የህትመት ሚዲያ ተቋማት ሃሳባቸውን በማጋራት ይታወቃሉ።

ቶም እንደሚገልጹት አሜሪካ ኢትዮጵያን የቀጠናው ወሳኝ አጋር አድርጋ እንደምታያት ስትገልጽ ብትቆይም ውሳኔው ኢትዮጵያን ይበልጥ ወደ ቻይና እንድትቀርብ ያደርጋታል በሚል የገለጹ ሲሆን ፤አሜሪካና ኢትዮጵያ ከነበራቸው የረጅም ጊዜ ግንኙነት አንጻር ይሄ አይነቱን ማእቀብ የመጣል ውሳኔ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው ብለውታል ፡፡

የማእቀብ መጣል የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ዲኤፍሲ) የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ኩባንያዎች ጥምረት ለቻይናዎቹ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ሁዋዌና ዜድቲኢ ጥቅም  በማይውልበት ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያን የቴሌኮም ዘርፍ  የ5 ጂ ኔትወርክ ጨረታ ተወዳድረው ማሸነፋቸው በተገለጸ ማግስት መሆኑ አስገራሚነቱን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ላይ ማዕቀብ እና ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ማቋረጥን እንዲሁም የአለም ባንክ ብድርን እና የአለም የገንዘብ ድርጅት ድጋፎች እገዳን ያካተተ ውሳኔን ሲያሳልፍ ምክንያት ብሎ ያስቀመጣቸው ነገሮች በትግራይ ክልል በተደረገው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ እርዳታ ክልከላና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መሆናቸውን ተንታኙ አብራርተዋል፡፡

ባለፈው ህዳር ወር በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ደም አፋሳሽ ግጭት ተከትሎ የተጣለው ማእቀብ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስለመሆኑ ያብራሩት ተንታኙ በግጭቱ ምክንያተ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ፣ ሁለት ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከቤታቸው የተፈናቀሉ መሆኑን በመጥቀስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መደረጋቸውን የዜና ተቋማት ተቀባበለው ሲዘግቡ እንደነበር አንስተዋል ፡፡

በቀይ ባህርና በአካባቢው ሊከሰት የሚችለው ማንኛውም አለመረጋጋት የጎሳ ውጥረትን በማባባስ እንደ አልቃይዳ እና አል ሸባብ ያሉ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች እንዲያንሰራሩና በአካባቢው የሚኖር እንቅስቃሴን ሊያስቆሙ ይችላል በሚል ስጋት አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ወሳኝ አጋሯ አድርጋ ስትመለከት እንደቆየች ያብራሩት ተንታኙ አሜሪካ እንዲህ አይነቱ ተቃራኒ ውሳኔ ላይ እንዴት ልትደርስ እንደቻለች በጥያቄ መልክ አንስተዋል።

 የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ጉዳዩን በሚመለከት ለወሰደው እርምጃ ከኮንግረሱ የተወሰነ ጫና እንደተደረገበት ግልጽ ነው ያሉት ተንታኙ በዋናነት ግን ቻይና ቀደም ሲል ከአፍሪካ ሃገራት ጋር በፈጠረችው መልካም የሚባል ግንኙነት ያልተደሰተችው አሜሪካ በአህጉሪቱ የቻይና ተወዳዳሪ ሆና ለመቅረብ ባላት ፍላጎት የተነሳ ነው ብለዋል።

 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ የናይጄሪያና የኬንያ መሪዎችን  ባነጋገሩበት ወቅት የአፍሪካ አገራት ቻይናን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመለከቷት ያስጠነቀቁበት ንግግራቸው የአሜሪካ  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዚህ አይነት የውድድር መነፅር የሚታይ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ተወስዷል ብለዋል ፡፡

ከቻይና በተቃራኒ ሁልጊዜም ስትራቴጂካዊ የበላይነቷን ለማረጋገጥ የምትሞክረው አሜሪካ በኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ላይም ተጽዕኖ ለማሳደር ያስችላሉ ያለቻቸውን ማዕቀቦች በመጣል የግሉን ዘርፍ ማጠናከርና የብድርና የእዳ ጫናዎችን እንደመደራደሪያ መጠቀም ላይ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል ተንታኙ።

 የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ዲኤፍሲ) እ.ኤ.አ በ2019 ሲመሰረት ታሳቢ ያደረገው የቻይናውን የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺቲቭን እንዲገዳደርና በታዳጊ አገራት የሚኖራትን ኢንቨስትመንት ድርሻ ከፍ ለማድረግ ቢሆንም ከቻይና በተቃራኒ የፖለቲካ እና የርዕዮተ ዓለም ተጽእኖው በመጉላቱ ምክንያት ሃገራት ከአሜሪካ የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ለአሜሪካን ስትራቴጂካዊ ምርጫዎች ተገዢነትን የግድ የሚል እንዲሆን ሲደረግ አንደኛው ማሳያም ሃገራት ድርጅቶቻቸውን ወደ ግል ሲያዛውሩ የግድ ለአሜሪካ ኩባንያዎች መሸጥ እንዳለባቸው የሚያስገድድ መሆኑ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

 የቻይናው ቤልት ኤንድ ሮድ መንግስት የያዛቸውን ኩባንያዎች የሚጠቀም ሲሆን በአንጻሩ የአሜሪካው ዲኤፍሲ  የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ የሚገፋፋ መሆኑን እንደ ምሳሌ ያነሱት ተንታኙ፣በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ኤፍ.ዲ.ሲ ከኢኳዶር መንግስት ጋር አስገዳጀ ስምምነት በመፈፀም ‹ክሊን ኔትወርክ› ለተባለውና የቻይና ኩባንያዎች የቴሌኮም ኩባንያዎች ለሚሰናበቱበት መርሃግብር እንዲሁም የኢካዶር የነዳጅ ኩባንያዎች ለአሜሪካውያን ባለሃብቶች ለሚተላለፉበት ሂደት ተግባራዊነት ሃገሪቱ የወሰደችውን  ዕዳ ለቻይና ለመክፈል ቃል መግባቱን አንስተዋል ፡፡

የብሪተን ዉድስ መስራች ተቋማት የሚባሉት የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት በኒዮሊበራል የኢኮኖሚ ፍልስፍና በመመራት በ1980ዎቹ ያወጧቸው የብድር አሰጣጥን የተመለከቱ አሰራሮች የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚዎችን በማዳከም የምእራባውያን ባለሃብቶችን ይበልጥ ያፈረጠሙ ሆነው መገኘታቸውን ያብራሩት ተንታኙ አሜሪካ ይሄንን ያህል ርቀት በመሄድ ሃገራትን የምታስገድድ ሆና እያለ ቻይና የአፍሪካን በእዳ ወጥመድ ዲፕሎማሲ እየያዘች ነው በሚል የመክሰሷ ተቃርኖ ትዝብት የሚፈጥር ነው ባይ ናቸው።  

በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ተጽእኖ ለማስፋት እንዲያስችላት የምትሰጠውን ብድር በቅድመ ሁኔታዎች ላይ እንዲመሰረት በማድረግና ማእቀቦችን በመጣል ላይ እንደምትገኝ ያስረዱት ተንታኙ አሜሪካ ለአፍሪካ ሃገራት የእዳ ስረዛና ማእቀብ የማላላት እርምጃዎችን ለመውሰድ የምታስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ ጸረ ቻይና አቋም ማራመድ ሲሆን እቅዱ አፍሪካ ውስጥ ያን ያህል ያልተሳካው ቻይና በቀላሉ በምትለቀው ካፒታልና በምትከተለው በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

 ይሄ አይነቱ ውሳኔ አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖራት እንቅሰቃሴ ላይ እንቅፋቶችን መፍጠሩ አይቀሬ ከመሆኑም በላይ የተጣለው ማዕቀብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የሚመራውን የኢትዮጵያን መንግሥት በማስከፋት ፊቱን ወደ ሌሎች እንዲያማትር ያስገደደዋል ያሉት ተንታኙ ኢትዮጵያ “ሉዓላዊነት” የሚለውን ሀሳብ ወደሚደግፉና አስፈላጊ የጦር መሳሪያዎችን ወደሚያቀርቡላት ቻይናና ሩሲያ ፊቷን ማዞራ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

ተንታኙ ሃሳባቸውን ሲቀጥሉ ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራት የአሜሪካን ኢንቨስትመንት ቢጠቀሙም በውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነቷ ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ስለማይፈልጉ ከቻይና ጋር የሚያደርጉትን ትስስር በበዙ እጥፍ እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው በመሆኑ አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ቻይና በቅርብ እየተከታተለች መሆኑን ገልጸዋል።

ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች አዲሱ አፍሪካን የመቀራመት እንቅስቃሴ የሚል ስያሜ ሊሰጡት እንደሚችሉ ያብራሩት ተንታኙ የአፍሪካ ሃገራት ራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት መካከል ራሳቸውን በአንደኛው ልእለ ሃያል መዳፈ ውስጥ ሊያገኙ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑንም አስረድተዋል።

ያም ሆነ ይህ አሜሪካ ኢትዮጵያን በሚመለከት ሃገሪቱንና መንግስትን ማዳከም የሚል ግልፅ የሆነ ስትራቴጂ ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ ስትሆን አላማዋም የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንቅፋት እንዳይፈጠር ማእቀቦችን በመጣል ሃገሪቷን በራሷ አምሳል መቅረጽ ላይ ያተኮረ መሆኑን ያብራሩት ተንታኙ የውሳኔዎቹ ውጤቶቹ ምን እንደሚሆኑ እና በአፍሪካ አህጉር የመጨረሻው አሸናፊ የትኛው ልዕለ ኃያል እንደሆነ የሚያሳየው ጊዜ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም