ኢትዮጵያ የኬሚካል ጦር መሳርያ መጠቀም የሚከለክለውን ሕግ በማስፈጸም ድርጊቱንም በግንባር ቀደምነት ከሚያወግዙ አገራት አንዷ ናት--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኬሚካል ጦር መሳርያን መጠቀም የሚከለክለውን ሕግ በማስፈጸምና ድርጊቱንም በግንባር ቀደምነት ከሚያወግዙ አገራት አንዷ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የቴሌግራፍ ዘጋቢ ዊል ብራውን በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻን ተከትሎ ባወጣው ዘገባ “መንግስት በትግራይ ክልል የኬሚካል ጦር መሳርያ ተጠቅሟል” በሚል ላሰራጨው የተሳሳተ ጽሁፍ የመረጃውን ሐሰተኛነትና ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን ገልጿል።

በመግለጫውም “ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ የጦር መሳሪያዎችንና በአለም አቀፍ ደረጃ በስምምነት የተቀመጡ ጸረ ኬሚካል መሳሪያ ድንጋጌዎችን በግንባር ቀደምነት ከሚተገብሩ አገራት አንዷ ነት” ብሏል።

ኢትዮጵያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በማንኛውም ሁኔታና ቦታ ላይ መጠቀምን ታወግዛለች ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ አስቀድሞ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የመሰለ ሆን ተብሎ የተሳሳተና ኃላፊነት የጎደላቸው ሪፖርቶችን በተመለከተ ተጨማሪ ውጥረትን ከማባባስ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስታወቁን ገልጿል።

አሁን የተሰራጨው ሐሰተኛና ሃላፊነት የጎደለው ዘገባም በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ላይ ጫና ለማሳደር ከሚደረገው ጥረት ተለይቶ ሊታይ አይችልም ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም