በመጪው ነሐሴ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ይጠበቃል

3223

አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 በኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍሎች በመጪው ነሐሴ ወር  ነጎድጓድና በረዶ አዘል ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪው ወር ዝናብ ሰጪና አልፎ አልፎም ለወንዞች ሙላትና ለቅፅበታዊ ጎርፍ መከሰት ምክንያት የሚሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች እየተጠናከሩ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቅፅበታዊ ጎርፍ ምክንያት የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መንሸራተት፣ የሰብል ማሳዎች በውሃና በደለል መሸፈን፣ የአረም መስፋፋት፣ የሰብል በሽታዎችና ተባዮች መከሰት ሊኖር የችላል ተብሎ ይጠበቃል።

በመሆኑም ለዚህ ዓይነቱ ጉዳት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አደጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ሊደረጉ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል።

ከወንዞች ሙላት ባሻገር በአንዳንድ ቦታዎች በሚጥለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ከፍተኛ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል የአየር ትንበያው አመላክቷል

በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢልባቡር፣ በሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ እንደዚሁም  በአዲስ አበባ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራል።

ከዚህም ሌላ የአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ባህርዳር ዙርያ፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ እንደዚሁም ሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች  የሚጥለው የክረምት ዝናም ይቀጥላል።

የትግራይ፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ዞኖች፣ ከደቡብ ክልል የከፋ፣ የቤንች ማጂ፣ የጉራጌ፣ የሀድያ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋና የሲዳማ ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎች ስርጭቱ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለቅፅበታዊ ጎርፍ መከሰት መንስኤ ሊሆን የሚቸል ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ ኤጀንሲው አመልክቷል።

ድሬዳዋና ሐረር፣ የአፋር፣ የአርሲና የባሌ ዞኖች፣ የጅግጅጋና የሽነሌ ዞኖች እንደዚሁም በአንዳንድ የደቡብ ኦሞ፣ የሰገን ህዝቦችና የቦረናና የጉጂ ዞኖች ከሚኖራቸው እርጥበት አዘል አየር በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ተበሎ ይጠበቃል።

በመጪው ወር የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ አየር ይኖራቸዋል።