የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ ይወሰዳል ..የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ

2754

ድሬዳዋ ሀምሌ 26/2010 የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ድብቅ ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን አስታወቁ።

ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ወቅታዊ ጉዳይን  አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በድሬዳዋ የራሳቸው ድብቅ ዓላማ ያነገቡ አካላት ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን የግጭት መነሻ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው።

በእዚህም አንድ ብሔር ከሌላው ጋር እንደተጋጩ አስመስለው የውሸት መረጃ የያዘ ወረቀት በመበተንና በሶሻል ሚዲያ በማስተላለፍ ወጣቱን ለግጭት እያነሳሱና የከተማውን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ የተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳምንት ወጣቶችን በማደራጀትና በተለያዩ ጥቅሞች በመደለል፤ አንዳንድ ባለንብረቶችም ተሽከርካሪያቸውን በመስጠት የከተማው ሰላምና ፀጥታ እንዲደፈርስና ጥፋት እንዲፈፀም ትብብር በማድረግ ላይ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ወጣቱ ምንም ዓይነት የስለት መሳሪያ ይዞ ከመንቀሳቀስ መቆጠብና ለሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንዲወጣ ያሳሰቡት ከንቲባው የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ተደራጅተው ወጣቱን ሊያስተምሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከንቲባው እንደተናገሩት ድብቅ ዓላማ አንግበው ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የሚሯሯጡ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፍትህ አካላት መረጃና ማስረጃ እያሰባሰቡና ጉዳዩን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

እንደከንቲባው ገለጻ በእሁኑ ውቅት በአራቱም የከተማው አቅጣጫ ሁሉንም የፀጥታ አካላት ያካተተ ጠንካራና የተቀናጀ የፀጥታ ኮማድ ፖስት ተቋቁሞ የህብረተሰቡን ሰላምና ድህነት ለማስከበር መንቀሳቀስ ጀምሯል።

“ኮማንድ ፖስቱ በድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚመራ ገልጸው ኮማንድ ፖስቱ ችግር ከተፈጠረ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል፡፡

በመግለጫው ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ በበኩላቸው የአገሪቱ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ  በፍቅር ፣በአንድነትና በመደመር ጉዞ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ሰፊ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የህዝቦችን የጠነከረ አንድነትና ፍቅር የማይፈልጉ አካላት ወጣቶችን ተገን በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰላም እንዲደፈርስ እሳት በመለኮስ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በድሬዳዋ ችግር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ሁሉም ነዋሪ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ መከላከል  እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አቶ አብደላ ገለጻ ባለፉት ጥቂት ቀናት በድሬዳዋ የታየው የሰላም መደፍረስ ድብቅ ዓላማ ባነገቡ አካላት የተፈጠረ እንጂ የድሬዳዋ ወጣቶችን የማይወክልና ከነሱ ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ወጣቶች ይህን መሠረታዊ ችግር በመረዳት ድብቅ ሴራ ያነገቡ አካላት ሰለባ መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

የሆቴል፣ የመኝታ፣ የቤት ኪራይ፣ የታክሲና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩም ምክተል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡