በአዳማ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ በማዘጋጀት የተሰማራ ግለሰብ ተያዘ

931

አዳማ፣ ግንቦት 13/2013 ( ኢዜአ) በአዳማ ከተማ የተለያዩ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት የተሰማራ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ  ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው  በከተማው ቀበሌ አስር በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው።


ፖሊስ የፍተሻና መያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት በማውጣት ዛሬ ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ላይ በግለሰቡ  መኖሪያ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በርካታ ሀሰተኛ ሰነዶችና ማተሚያ ማሽኖች መገኘታቸውን ገልጸዋል ።


ማተሚያና የወረቀት መቁረጫ ማሽን፣ ከ6ኛ ክፍል እስከ ዲግሪ ድረስ ያሉ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችና መንጃ ፍቃዶች መገኘታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በተለያዩ በዝርፊያና ሌብነት ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች የተዘጋጀ መታወቂያና ሌሎችም ሀሰተኛ ሰነዶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።


በተጨማሪም የመሬትና የካርታ መለያ ቁጥሮች፣የውክልና የድጋፍ ደብዳቤዎች፣ የውልደትና የሞት ማስረጃዎች፣ የተሽከርካሪ ሊብሬዎችና ድክላራሲዮን፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች መታወቂያ በኤግዚቢትነት መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቡ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎችን በመስራትና በማሰራጨት የተሰማራ መሆኑን ፖሊስ  ቀድሞ መረጃ የደረሰው መሆኑን  ገልጸዋል።


የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል ለአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ አሳልፎ መስጠቱን ኮማንደር አስቻለው አስታውቀዋል ።