የቴክኖሎጂ ሽግግርን ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

99

አዲስ አበባ፣  ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማነት የትምህርትና ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አስገነዘቡ።

"የተጠናከረ ትስስር ለምርት ጥራትና ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ የትምህርትና ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ትስስር ቀጣናዊ ክላስተር ውይይት ተካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ተግባራዊ ለማድረግ የተቋማት ትብብርና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በውይይቱ ላይ አስገንዝበዋል።

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢኖቬሽን ልማት ሂደትን ለመምራት ቅንጅታቸው መጠናከር አለበት ብለዋል።

ትስስሩን በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎችም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ማስፋት የአገሪቱን ዕድገት እንደሚያፋጥን ፕሮፌሰር አፈወርቅ አመልክተዋል።

በቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመቅዳት፣ ለማላመድና አዳዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ትስስሩ ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገልጸዋል።

ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሥራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አስረድተዋል።

በሚኒስቴሩ የተቋማት ትስስርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ጌታቸው ተፈራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና ኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ በምርምር ስራዎች ማገዝ አለባቸው ብለዋል።

ይህን ለማገዝ ሚኒስቴሩ የተዘጋጁ የትስስር ፖሊሲ፣ ደንብና መመሪያዎችን በማስፀደቅ ወደ ተግባር ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተቋማቱንና የኢንዱስትሪዎችን ትስስር በማጠናከር የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የጋራ ዕቅድ ክትትልና ስርዓት መዘርጋትና መተግበር እንዲሁም ችግሮች መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በዘርፉ ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት በመሥጠት ውጤታማ መሆን ይቻላል ያሉት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ቀጣናዊ ክላስተር ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ንጉሴ ናቸው።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ አስተባባሪ ወይዘሪት ሕይወት ፈለቀ በበኩላቸው ተቋሙ የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የማሽኖች ማምረት፣ ለኅብረተሰቡ ታዳሽ ኃይል ማቅረብና የማማከር አገልግሎቶችን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም