በሴቶች ፖሊሲ ላይ ያለውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት የማሻሻያ ሥራ እየተሰራ ነው

82

አዲስ አበባ፣  ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ በሴቶች ፖሊሲ ላይ ያለውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት የማሻሻል ሥራ መጀመሩን የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ ተናገሩ።

የፖሊሲው የሕግ ክፍተት በዘርፉ ለሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በቂ ምላሽ እንዳይሰጥ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ያለውን "የኢትዮጵያ ሴቶች ፖሊሲ" ለመከለስ ባካሄደው ጥናት ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

ሚኒስትሯ ባለፉት 28 ዓመታት እየተተገበረ የሚገኘው ፖሊሲው በአገሪቱ በሴቶች እኩልነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

"ይሁንና ወቅቱ በሁሉም ዘርፍ መሻሻልና ዘመናዊ አሰራርን መከተል የሚጠይቅ በመሆኑ ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈልጋል" ብለዋል።

በተለይ ለውጡን ተከትሎ በአገሪቱ ሴቶችን ለማብቃትና ወደፊት እንዲመጡ ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ቀጣይ ለማድረግ ፖሊሲውን ማሻሻልና ማዘመን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከሴቶች ጥቃት፣ ከፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ አሁንም መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመው "በሚፈለገው መልኩ እንዳይሰራ ፖሊሲው አሳሪ ነው" ብለዋል።

በተለይ በቀጥታ በሕግ ምላሽ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በተዘዋዋሪና በተንዛዛ መልኩ የሚከናወኑ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ነው ሚኒስትሯ ያስረዱት።

እነዚህንና ተዛማች ጉዳዮችን የሚፈታ ፖሊሲ መቅረጽ እንዲቻል ፖሊሲውን የማሻሻል ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህም የተለያዩ አካላት ጥናት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ጥናቱ በውይይት ከዳበረና ማሻሻያ ከታከለበት በኋላ ፖሊሲው ተሻሽሎ እንዲዘጋጅ ይደረጋል ብለዋል።

ከኢንክሉድ ኦቬት የጥናትና ምርምር ተቋም የፖሊሲው አጥኚ ቡድን መሪ ወይዘሮ ኪያ ገዛኸኝ በተግባር ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፖሊሲ ሥራ ላይ መዋል በጀመረበት ጊዜ የተሻለና ለውጦች እንዲመጡ ያደረገ ነው።

ይሁንና በፖሊሲው የተካተቱ አብዛኞቹ አንቀጾች ተግባራዊ እንዲሆኑ አስገዳጅ መመሪያ አልተቀመጠም።

ይህም የአተገባበር ክፍተት ከመፍጠሩ ባሻገር በሕግ አግባብነት ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሲጓተቱና ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ተስተውለዋል ብለዋል።

በፖሊሲ ማሻሻያ ጥናቱ ትኩረት የሚሹ ዘርፎች ላይ በማተኮር ግብዓት የማሰባሰብ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ጾታዊ ጥቃት፣ የኢኮኖሚ እና የባለቤትነት ተጠቃሚነት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት።

በእነዚህ ዘርፎች ሴቶችን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግና ለሚደርስባቸው ማንኛውም ጉዳቶችና ጥቃቶች በቂ የሕግ ምላሽ ለመስጠት ፖሊሲውን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስሩ ከሴቶች በተጨማሪ የወጣቶችና ሕጻናትን ጉዳይ ስለሚመለከት "የኢትዮጵያ ሴቶች ፖሊሲ" የሚለው 'የስርዓተ ጾታ ፖሊሲ' ተብሎ ቢቀረጽ ተደራሽነቱን ሊያሰፋው ይችላል በሚል ጥናቱ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከነባሩ ፖሊሲ የተሻሉና ቀጣይነት ሊኖሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የቀድሞ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ በፖሊሲው የተካተተውና እየተተገበረ ያለው የሴቶች የልማት ፓኬጅ ኢኮኖሚያዊ ገቢያቸውን ስለሚያሳድግ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ እቴነሽ ዘለቀም ለጥናቱ በሴቶች ጉዳይ ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ግብዓት ማሰባሰብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ በፖሊሲ ክለሳው ላይ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በትኩረት እንዲሰራም አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም