"ኢትዮጵያ በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚገስስ የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን አልነበረም አይኖርም"... እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ መርሃ ግብር አዘጋጆች

71

ግንቦት 13/2013(ኢዜአ) "ኢትዮጵያ በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚገስስ የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን አልነበረም አይኖርም" ሲሉ የእጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ መርሃ ግብር አዘጋጆች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በያሉበት ሆነው ድምፃቸውን የሚያሰሙበት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው።

"እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ለአንድ ሠዓት መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መርሃ ግብር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቅጥር ግቢ ነው በይፋ የተጀመረው።

"ብሔራዊ ክብር በሕብር" የሚል ስያሜ ያለውን ይህን ንቅናቄ ያዘጋጁት የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ የሲቪክ ማሕበራትና ታዋቂ ግለሰቦች ናቸው።

"ግድቡ ገንዘቤ፣ ዓባይ ወንዜ!፣ ዓባይ ጸጋችን ነው፣ ኢትዮጵያ አትደፈርም አንንበረከክም" የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብተዋል።በመርሃ ግብሩ ላይ "ክብርና ሉዓላዊነታችንን አትንኩ የምንለው በአያቶቻችን መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች እና በዋጋ የተረከብናት አገር በመሆኗ ነው" ሲሉ አዘጋጆቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ኢትዮጵያ "በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚገስስ የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን አልነበረም አይኖርም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ "ከራሷ አልፋ ለሌሎች ነፃነትን ያስተማረች፤ አልገዛም ባይነትን በተግባር ያሳየች፤ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ነች" ሲሉም ተናግረዋል።

"ከአያቶቻችን የወረስነው ልበ ሙሉነት፣ ሌላውን ማክበርና ቀና ብሎ መራመድን እንጂ ለፍርሃት ማቀርቀርን አይደለም" በማለትም ነው የገለጹት።

በመሆኑም ለዘመናት የኖርንበትና የተጋመድንበትን የአንድነት መሰረት የሚገዳደርና ክብራችንን የሚገረስስ ተግባራትን አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም