የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማዘመን ተወዳዳሪነታቸው ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል

60

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውንና ተቀባይነታቸውን እንደሚያሳድገው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ተግባራዊ ያደረገውን ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት የሚያዘምንና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሺፈራው ሰለሞን ገልጸዋል።

እስካሁን ሲሰራበት የቆየውን የሒሳብና የሰው ሃይል አያያዝ ሁኔታ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በመቀየር ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑንም ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂው ከፍተኛ የመንግስትና የሰው ሃብት የፈሰሰባቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስተዳደርና ቀጣይነት ያለው እድገት የሚያመጣ ነው ብለዋል።

የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሱራፌል ሺመልስ በበኩላቸው በፓርኮች የሚተገበረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ የኮርፖሬሽኑን የሰው ሃብትና ገንዘብ በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

በዋናነትም የፋይናንስ መስኩንና የግዥ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች አሰራሮችን በማዘመን ዘርፉ የሚያስተዳድረውን ግዙፍ ሃብት በሚፈለገው መልኩ ስራ ላይ ለማዋል እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

እስካሁን ኮርፖሬሽኑ ሲጠቀምበት የነበረው ቴክኖሎጂ አነስተኛ አቅም ነበረው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ አዲሱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ወደ ወረቀት አልባ አሰራር የሚያሸጋግረው ይህ ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ፍቅሬ ታደገኝ ፕሮጀክቱ አገሪቱ ያላትን ውሱን ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ዓለምአቀፍ የገንዘብ ስርዓት በፕሮጀክቱ የተተገበረ በመሆኑ በተለይ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚወጡ ሪፖርቶች ተዓማኒነታቸው ከፍ እንዲል ማድረጉን አመልክተዋል።

ፓርኮቹ ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው አሰራር በአነስተኛ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በሒደት የሚፈጠረውን እድገት በአግባቡ ለማስተናገድ ክፍተቶች ነበሩ ነው ያሉት።

በመሆኑም አዲሱ ቴክኖሎጂ ፓርኮችን ለማዘመንና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም