የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

101

ጎባ፤ ግንቦት 13/2013 (ኢዜአ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው “አጋርነት ለተሻለ ለውጥ“ በሚል መሪ ሀሳብ በባሌ ዞንና አካባቢዋ ከሚገኙ  ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በሮቤ ከተማ አካሄዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ ማህበረሰብ አቀፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ሽፋ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ተግባር በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከስራዎቹም መካከል ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም  በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየት መፍትሄዎች ለመሻት ጥረት እያደረገ  መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዶክተር ሀሰን እንዳሉት፤ በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት በተለያዩ የትኩረት መስኮች ከተሰማሩ የመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው የምክክር መድረክ በቀጣይነት በጋራ አብሮ ለመስራት ትልቅ አቅምና እድል ይፈጥራል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄደውን የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ተግባራት ውጤታማና ቀጣይነት እንዲኖራቸው የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተመቻቸው መድረክ በተበታተነ መልኩ በባለድርሻ አካላቱ ሲካሄድ የነበሩትን የልማት ስራዎች በታቀደና በተጠና መልኩ አብረው ለመስራት እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ተመሳሳይ ስራን በተለያዩ ተቋማት በማከናወን  ይባክን የነበረውን በጀት በማስቀረት በውጤታማ ተግባራት በጋራ እንዲፈጸሙ የምክክር መድረኩ ሌላው ዓላማ  መሆኑን አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በሪሶ፤ ማዕከላቸው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማትን በመጨመር የምግብ ዋስትናው እንዲያረጋግጥ ከ80 የሚበልጡ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን ለተጠቃሚው አድርሷል ብሏል፡፡

ከዩኒቨርሲውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተፈጠረው መድረክ በፊት የሚሰሩትን ተግባራት በማጠናከር ቀጣይነትና ውጤታማ እንዲሆን ይረዳናል ብለዋል፡፡

መድረኩ በባሌ አካባቢ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሻሻል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን የቱሪዝም ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሽብሩ አብዶ ናቸው፡፡

በተለይ በዞኑ የሚገኘውና  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም /ዩኔስኮ/ በጊዜያዊ መዝገብ ላይ የሰፈሩት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና ድሬ ሼህ ሁሴንን ታሪካዊ ስፍራ በማልማት ረገድ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሮቤ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ከባሌ ዞንና አካባቢው የተውጣጡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በመቀበል በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች እያስተማረ  ከመሆኑም በላይ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የምርምር ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም