የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች መፍታት አለበት ...የክልሉ ምክር ቤት አባላት

83
ጋምቤላ ሀምሌ 26/2010 የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሰባት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የወንጀልና የፍታብሔር መዝገቦች ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ላይ ውይይት አድርገዋል። የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ወቅት እንዳሉት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉ ህዝብ በፍትህ አገልግሎት አሰጣት ላይ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። በተለይም ፍርድ ቤቱ በመዝገብ አያያዝ፣ በውሳኔና ዋስትና አሰጣጥ እንዲሁም በዳኞች አቅም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት በኩል ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጹት። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ኡማን ኡጋላ እንዳሉት በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ያሉባቸውን ውስንነቶች በመለየት ህዝቡን የተሻለ የፍትህ ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ "በተለይም በመዝገብ አያያዝና በፍትህ ተደራሽነት ላይ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ መሰራት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡ "በክልሉ ያለው የዋስትና አሰጣጥ የፍትህ አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ችግሩን ለመፍታት መስራት አለባቸው" ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ማህበር ኮር ናቸው፡፡ በተለይ በገንዘብና በሌሎችም ከባድ ወንጀሎች ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የሚውሉ ግለሰቦች ዋስትና ከማግኘታቸው በፊት የወንጀሉ ክብደት በደንብ የሚታይበት ሁኔታ ሊጣራ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታየው የውሳኔ አሰጣት ከአድሎ የጸዳ አለመሆኑን የገለጹት ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ፓል ቱት ናቸው። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ችግሩን በመፍታት ሁሉም አካል ፍትሀዊ ውሳኔ የሚያገኝበትና መልካም አስተዳደር የሚሰፍንበትን መንገድ መፍጠር እንዳለበት አሳሰበዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችም ያሉባቸውን ክፍተቶች ለማረምና በቀጣይ ለህብረተሰቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንአቶ ኡቦንግ ኡጁሉ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ በሰጡበት ውቅት እንዳሉት ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጡት ከተለያዩ አካላት ለሚቀርቡ መዝገቦች ህጉን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ህዝቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ ዳኞችን ባላቸው የሥራ አፈጻጸም እያየ የሚሾሙበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በውሳኔ አሰጣት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ዳኞች ሙሉ ለሙሉ የሉም የሚል እሳቤ እንደሌለ አመልክተዋል። ችግሩን በመከላከል ህዝቡ የተሻለ ፍትህ እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኡቦንግ፣ ለስኬታማነቱ ሁሉም የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤት ለማንም ወገንተኛ ሳይሆን ሁሉንም አካላት ህጉን መሰረት በማድረግ የፍትህ አገልግሎት እንደሚሰጥና የዋስትና አሰጣጡም በህጉ መሰረት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ኡቦንግ እንዳሉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ8 ሺህ 315 የወንጀልና የፍታብሔር መዝገቦችን ውሳኔ ለመስጠት አቅዶ ለ7 ሺህ 564 መዝገቦች ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም