ኤጀንሲው የተናበበና ፈጣን መረጃ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ከሁለት ተቋማት ጋር ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው የተናበበና ፈጣን መረጃ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ከሁለት ተቋማት ጋር ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2013(ኢዜአ) የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተናበበና ፈጣን መረጃ ለመስጠት የሚያስችል የአሰራር ስምምነት ከጤና ሚኒስቴርና ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጋር ተፈራረመ።
የተቋማቱ ስምምነት የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በቅንጅት በመስራት ፈጣንና ተዓማኒ መረጃ ለማድረስ መሆኑን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሙጂብ ጀማል ተናግረዋል።
በአንድ ተቋም ተጀምሮ ስራው በአንድ ተቋም የሚያልቅ ባለመሆኑ ከተቋማቱ ጋር የተደረሰው ስምምነት የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠትና ተቋሙንም ለማዘመን እንደሚረዳ ነው የገለጹት።
የኩነት ስታስቲክስ ያለበት ደረጃ ባለፈው ዓመት ጥናት ተካሂዶ እንደነበር አስታውሰው፤ የዜጎች ምዝገባ በተገቢው መንገድ እንደማይካሄድ መረጋገጡን አመልክተዋል።
ተቋማት ተቀናጅተው ባለመስራታቸው ችግሩ እንደሚከሰት ጥናቱ አሳይቷል ያሉት አቶ ሙጂብ፤ በጥናቱ የተለዩትን በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በሰው ኃይል ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫ ማሳየቱን አብራርተዋል።
ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በሚተገበረው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ''ሁሉም ሰው የሚታወቅባት ኢትዮጵያ'' የሚለውን መሪ ሃሳብ ለማሳካት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ስምምነቱን ያደረጉት ተቋማት ተወካዮችም ተዓማኒና ፈጣን መረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ለመወጣት ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ለውጭ ሀገር ዜጎች የልደትና የሞት ማስረጃዎችን በመስጠት የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ይሰጥ የነበረ መሆኑንና ህጋዊ አሰራር ተከትሎ እንዲሰራ ለማድረግ የተጀመረው ግን በ1934 ዓ.ም እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ ከተጀመረው የሪፎርም ስራዎች ውስጥ አንዱ የኢሚግሬሽን አገልግሎት በመሆኑ አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶታል።
ተቋሙ ከወሳኝ ኩነት ጋር በመዋሀድ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በሚል ስያሜ እንደ አዲስ እንዲቋቋም በማድረግ ቀጣይነት ባለው የሪፎርም ስራዎች አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።