ኩባንያው ተመሳስለው በሚመረቱ ምርቶች ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል

78
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 በገበያው ላይ ተመሳስለው በሚመረቱ የመጸዳጃ ቤትና የገበታ ወረቀቶች ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁን ማምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አስታወቀ። የኩባንያው የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብደላ አህመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ተመሳስለው በሚመረቱ የመጸዳጃ ቤትና የገበታ ወረቀቶች ምክንያት የኩባንያው ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል። ኩባንያው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የመጸዳጃ ቤትና የገበታ ወረቀቶች እንዲሁም የመማሪያ ደብተሮችን በጥራት እያመረተ ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል። በየዓመቱ በአማካይ ከ 8 እስከ 9 ሚሊዮን ብር ግብር ሲከፍል መቆየቱን የጠቆሙት አቶ አብደላ በማህበራዊ አገልግሎትም ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኩባንያው ተመሳስለው በሚሰሩ ምርቶች ምክንያት በገበያ ውስጥ የመቆየት ሁኔታው አደጋ ላይ  መውደቁን ጠቁመዋል። ኩባንያው ሲመሠረት ለ50 ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አብደላ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ወደ 200 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል። እንደ አቶ አብደላ ገለጻ ባለፉት ዓመታት ኩባንያው በህብረተሰቡ ዘንድ ያፈራውን መልካም ስምና ተወዳጅነት በመጠቀም በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚፈልጉ አካላት ከኩባንያው ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያለውን የመጸዳጃ ቤት ወረቀት አርማና ስም ጋር እጅግ ተቀራራቢ ስያሜ በመጠቀም ገበያውን በስፋት ተቀላቅለዋል። ''በኩባንያው ላይ እየደረሰ ያለውን በሚሊዮን የሚቆጠር ኪሳራና ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ጥብቅ ክትትል ባለመደረጉ ጉዳቱን መከላከል አልተቻለም'' ብለዋል። ኩባንያው ለሆቴሎች 130 ግራም፣ ለሱፐር ማርኬትና ለመደብር ደግሞ 100 ግራም የመጸዳጃ ቤት ወረቀት የሚያቀርብ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ 70 እና 80 ግራም ያላቸው ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ተመሳስለው ወደ ገበያ መግባታቸውን ኩባንያው ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ምርቶች ወደ ገበያ በመግባታቸው የመጸዳጃ ቤት ወረቀት ምርቱ እየቀነሰ ከመምጣቱም ባሻገር በመጋዘን ውስጥ ከፍተኛ የምርት ክምችት መፈጠሩን አስረድተዋል። በኩባንያው ላይ እየደረሰ ያለውን የህልውና ችግር ለማስቀረት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም