በዞኑ አርሶ አደሮች ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የግብርና አስራሮችን እየተጠቀሙ ነው

81
ሽሬ እንዳስላሴ ሃምሌ 26/2010 ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የተሻሻሉ የግብርና አስራሮችን ተጠቅመው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፈው የምርት ወቅት ጤፍን ጨምሮ የተለያየ የሰብል ዓይነት በመሰመር በመዝራት የተሻለ ምርት ማግኘት ችለዋል፡፡ አርሶ አደር ቄስ ሳሙኤል ተወልደ  በታሕታይ አዲያቦ ወረዳ የአደመይቲ  ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  " ከሁለት ዓመታት በፊት በብትንና ዘመናዊ የምርት ግብአትን ሳልጠቀም ማሳዬን በዘር በመሸፈን ከሄክታር የማገኘው የሰሊጥ ምርት መጠን ከአራት ኩንታል አይበልጥም ነበር"ሲሉ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ አምና ዘመናዊ የምርት ማሳደግያ ግብአት ተጠቅመው  በመስመር በመዝራት ካለሙት  አንድ ሄክታር መሬት  12 ኩንታል የሰሊጥ ምርት መግኘታቸውን ተናግረዋል። በተያዘው  የምርት ዘመንም ማዳበሪያና ሌሎችንም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ባላቸው ሶሰት ሄክታር ማሳቸው ላይ ሰሊጥ፣ ማሽላና ጤፍ  ዘርተው እየተንከባከቡ ናቸው፡፡ ከዚህም  የተሻለ  ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር  ወይዘሮ አዜብ ተወልደብርሃን በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በምርጥ የሰሊጥ ዘር በመስመር  እየሸፈኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ " በመስመር መዝራት የተጨማሪ ጉልበትና የሰው ሃይል ቢጠይቅም ውጤቱ አመርቂ እንደሆነ ካለፈው ተሞክሮ ማየት ችያለሁ " ብለዋል። ዘንድሮም ማሳቸውን  የምርት ማሳደጊያ ግብአት በወቅቱ ተጠቅመው ምርታማነታቸወን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ጤፍ በመስመር መዝራት ከጀመሩ ከሁለት ዓመት ወዲህ ምርታቸው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በታህታይ ቆራሮ ወረዳ የበለስ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር አብራሃለይ መሓሪ  ናቸው፡፡ ባለፈው የምርት ወቅት ከአንድ ሄክታር ማሳ ላይ 21 ኩንታል የጤፍ ምርት መሰብሰብ ችለው እንደነበር አስታውሰዋል። በተያዘው የምርት ወቅትም አንድ ሄክታር ማሳቸው በጤፍ ሰብል በመስመር በመዝራት ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰሩ ነው፡፡ በመደባይ ዛና ወረዳ የባህራ  ቀበሌ አርሶ አደር አዳነ አብርሃ እንዳሉት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን መጠቀም ከጀመሩ ከሦስት ዓመት ወዲህ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ  ማምረት ችለዋል፡፡ በተያዘው የምርት ዘመንም ሶሰት ሄክታር ማሳቸው በተለያየ የሰብል ዘር  እያለሙ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ እንዳመለከቱት የግብርና ባለሙያዎችም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው፡፡ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ በተያዘው የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብል ለማልማት  ከታቀደው 320 ሺህ 400 ሄክታር ማሳ እስካሁን ከ171 ሺህ ሄክታር በላይ ታርሶ በዘር መሸፈኑን በዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የአኮኖሚ ዘርፍ የስነ አዝርዕት ባለሙያ አቶ አዱኛ ገብራይ ገልጸዋል። ቀሪውን ማሳ ለማልማት ስራው መቀጠሉንና  እስካሁን በዘር ከተሸፈነው ውስጥም  57 ሽህ 465 ሄክታሩ በመስመር የተዘራ መሆኑን አመልከተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም