በክልሉ በ2010 በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት ተግባራት ከህዝብ ፍላጎት አንጻር በቂ አይደሉም - አቶ አሻድሊ ሐሰን

52
አሶሳ ሃምሌ 26/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2010 በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት ተግባራት ከሕብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር በቂ አለመሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተናገሩ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ የ2010 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላትን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው። አቶ አሻድሊ ብእዚህ ወቅት እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉን ህዝብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ በእዚህም በ2009 / 2010 የምርት ዘመን ከ20 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱንና ይህም ቀደም ካለው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከ125 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ 145 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከ2005 ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያዎች ግንባታ ሥራን ለማጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም ግንባታቸው የተጓተቱ መኖራቸውን አቶ አሻድሊ ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡ እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች ብዙም ውጤት አልተመዘገበባቸውም፡፡ በመንገድ ማስፋፋትና ጥገና፣ በገቢ አሰባሰብ፣ የፍትህ አገልግሎትን በማጠናከርና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች ቢኖሩም ከፍላጎቱ አንጻር በቂ አይደለም። በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም አንዳንዶቹ ከዕቅድ በታች የተፈጸሙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ የአመራሩ አቅም ውስንነት፣ የክህሎት ማነስ እንዲሁም ፖሊሲና ስትራቴጂን በሚገባ ተረድቶ አለመስራት ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያት መሆናቸውንም ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡ በተያዘው የ2011 በጀት ዓመት ችግሮቹን የሚፈቱና የልማት ተግባራትን በሚገባ ለማከናወን የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም አቶ አሻድሊ አመልክተዋል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የጉባ ወረዳ ህዝብ ተወካይ አቶ ሆስኒ ሐሰን እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የህዝብን ሃብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል በኩል የሚስትዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ብድርና ቁጠባ ተቋም አሰራር ሰርተው መለወጥ የሚፈልጉ የወረዳው ነዋሪዎችን የሚደግፍ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ሆስኒ እስካሁንም ከወረዳ የሚያገናኝ መንገድ የሌላቸው ቀበሌዎች መኖራቸውን አመለክተዋል፡፡ ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ሱአድ ሙሳ በበኩላቸው " አሁን በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ያሉብንን ውስንነቶች ቀርፈን በበለጠ እንድንሰራ አቅም ይፈጥራል" ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም