በደብረ ብርሃን ከተማ ሀሰተኛ ሳሙና ሲሸጥ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

660

ደብረ በርሃን ግንቦት 7/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረብርሃን ከተማ ሳሙና መሰል ጠጣር ነገር ሲሸጥ የተገኘ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታየ ኃብተጊዮርጊስ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ነው፡፡

ፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ባካሄደው ፍተሻ 250 ካርቶን ሳሙና መሰል ጠጣር ነገር ተይዟል፡፡

“የተያዘው ሳሙና መሰል ጠጣር ነገር አንዱ 130 ግራም እንደሚመዘን የሚጠቁም ፁሁፍ ያለው ነው” ያሉት ምክትል ኮማንደሩ፡፡

ሳሙና መሰል ነገሩ ሲታጠብበት አረፋ አይወጣውም፤ ሲፈነከትም አሸዋ መሰል ጠጣር ነገር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተያዘው ናሙናም ለኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ለምርመራ መላኩን አስታውቀዋል፡፡

በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ ብስራት ዓለሙ እንደገለጹት የተበላሹ ሸቀጦችንና ባእድ ነገሮችን አመሳስለው ለገበያ የሚያቀርቡ ህገወጥ ጋዴዎችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ለሚያደርገው ጥረት ነዋሪውና ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

አቶ ደሳለኝ ሀጎስ በበኩላቸው ሳሙና መሰል ጠጣር ነገሩ በባሶና ወራና ወረዳ ጎሸባዶ ከተማ በአንድ ብር  ሦስት ሲሸጥ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ እስከ ገጠር ዘልቆ በመግባት የተሰራጨው ሳሙና መሰል ነገር በሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሊሰበሰብ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በከተማው ከሳምንት በፊት ለመፈጨት የተዘጋጀ 50 ኩንታል የተበላሸ በርበሬ መያዙን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል፡፡