የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰሜን አሜሪካ ቆይታ በተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተደንቋል

70
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት አገራዊ አንድነት ከማምጣት አንጻር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተፎካካሪ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተዘዋውረው በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መቀመጫቸውን ውጭ ካደረጉ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራዎቹ ሲደርሱም ሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ደማቅ አቀባበል አግኝተዋል። በዚሁ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየት የሰጡ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችም "ጉዞው ስኬታማና የሚደነቅ ጉዞ ነበር" ብለዋል። በተለያዩ ኃይሎች መካከል በቆየው አለመግባባትና ቁርሾ ምክንያትም ውጭ የነበሩ ዜጎች በአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የለውጥ ሂደት ላይ ማበርከት የሚገባቸውን አስተዋጽኦ እየተጫወቱ አልነበረም ብለዋል። አሁን ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረጉ ውይይቶችና የተፈጠረው ድባብም የአገር አንድነት ከማጎልበት አንጻር የጎላ ፋይዳ ያለው ስኬታማ ጉዞ ነበር ብለዋል። ከኦዴግ ዶክተር ዲማ ነገዎ እንዳሉት  ''አብዛኛው ውጭ ያለው ማህበረሰብ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ፣ ያለውን ስርዓት በመጥላት ነው ወደ ውጭ የተሰባሰበው፤ አንዳንዱም ከኢኮኖሚ አንጻር የወደ ፊት ተስፋ በማጣትም የሄደ አለ። አብዛኛው የመንግስት ተቃዋሚ ነበር ማለት ይቻላል። ግን ይሄ ግንኙነት ወደ አዎንታዊ ግንኙነት እንዲለወጥ ለማድረግ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ በጎ ይመስለኛ።'' አቶ ደሳለኝ ምኒሻ ከቅንጅት''ከመቶ 99 ፐርሰንት በሚዲያ እንደተከታተልነው ደስ የሚልና ከጠበቅነው በላይ ነበር። ይህ ደግሞ ምንን ያመላክታል እውነት አገራችን የሚትለወጥበት ጊዜና ሰዓት መሆኑ፣ በዲፕሎማሲ ደረጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ ምንያህል ጠንካራ እንደሆኑና የአገራችን ፖሊቲካ በሰፊው ማራመድ፤ የተበታተነውን አካል ወደ አንድነት ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ከምንም በላይ የሚያስደስትና ለእኛም ወኔ የሆነበት ሰዓት ነውና እኛም እንድንበረታ ለህዝባችን እንድንሰራ የሚያደርገን ነገር ነው” ብለዋል፡፡ ''በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው፤ ይህ ማህበረሰብ በፖሊቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው የሚገባውን አስተዋጽኦ እየተጫወተ አልነበረም ባለፉት 27 አመታት፤ እንዲሁም አፍራሽ በሆነ መንገድ ነው አስተዋጽኦ ሲያደርግ የነበረው። ይህ ኃይል ተሰብስቦ በአገሪቱ በኢኮኖሚም  ሆነ በፖሊቲካው ዘርፍ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። በዋናነት ግን የነበሩ ቅራኔዎች ቁርሾዎችን መቅረፉ ትልቅ ድል ነው።'' ያሉት ከኢዴፓ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ህዝቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን እሩቅ የመጓዝ ራዕይና ታላቅ አገር የመገንባት ዓላማ ተገንዝቦ የበኩሉን እየተወጣ አገር እንዲያረጋጋና አንድ የሚያደርጉ ነገሮች ብቻ ላይ እንዲያተኩርም መክረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም