የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የተለያዩ የግብርና ሪፎርሞች እየተካሄዱ ነው

80

ግንቦት 8/2013 (ኢዜአ) የግብርና ሚኒስቴር በግብርና ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የተለያዩ ሪፎርሞችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወንዳለ ሃብታሙ ለኢዜአ እንዳሉት በአገሪቱ የግብርና ሴክተር የሚካሄደው ሪፎርም በዋነኝነት አርሶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ያለመ ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ኃብት ያለው በመሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብት ለመሳብም በማለም እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርትና ምርታማነትን መጨመር የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የሉዓላዊነትም ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።  

ለአብነትም የስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በመስኖ የታገዙ ሰፋፊ ኩታ ገጠም የግብርና ልማት ፕሮጀክቶች  እየተተገበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም የፍራፍሬና የአትክልት ምርታማነት ሥራም እየተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርናው ሴክተር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሊፈስበት የሚገባ በመሆኑ ዘርፉን የማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ደግሞ በአበባና ፍራፍሬ፣ በእንሰሳት ተዋጽዖና በአትክልት ልማት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት አቅርቦትና ተያያዥ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ችግሮች ከክልል አመራር አካላት ጋር በመሆን እልባት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በኢንቨስትመንት አዋጅ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ የህንድ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሳኡዲ አረቢያ፣ የእስራኤልና የአሜሪካ ባለሃብቶች በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል።   

ለአብነትም ባለፈው ወር ብቻ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለመሳብ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ከ550 በላይ የግብርና መሳሪያዎች ከታክስ ነጻ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም