ፓርኩ በሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር መጠቀም ይገባል- ዶክተር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኩ በሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር መጠቀም ይገባል- ዶክተር አብይ አህመድ

ሠመራ ፤ ግንቦት 07/2013(ኢዜአ) የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ በመረቁበት ወቅት እንደገለጹት፤ የአፋር ክልል የብዙ እምቅ ተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ነው።
ከዚህም ውስጥ ክልሉ ያለውን ሰፊ ለም መሬትና የማዕድን ሀብት በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ከክልሉ አልፎ ለሃገር እድገት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
እነዚህን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች አልምቶ ሁለተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ ፓርኩ የማይናቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ፓርኩ የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅሞ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከመቀየር ባለፈ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ ጠንካራ የስራ ባህል በመገንባት በልማቱ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍና ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፤ ፓርኩ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሃብት ለመቀየር የሚያስችል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ፓርኩ ወደ ስራ ሲገባ በክልሉ እያደገ የመጣውን የወጣቶች የስራ እድል ጥያቄ መልስ በመስጠት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እውን እንዲሆን የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ የክልሉና ፌደራል መንግስት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ስነርዓት የፌዴራልና ክልል መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።