በመዲናዋ በቀን ሁለት ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ የምገባ ማዕከል ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በቀን ሁለት ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ የምገባ ማዕከል ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ በተለምዶ ሱማሌ ተራ በሚባለው አካባቢ የተገነባው የተስፋ ብርሃን አሙዲን የምገባ ማዕከል ዛሬ በይፋ ስራ ጀመረ።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕና በዳሸን ባንክ የተገነባውን የምገባ ማዕከል ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ ስራ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ወቅት አንድ ሺህ ተመጋቢዎች የተገኙ ሲሆኑ ከነገ ጀምሮ ሁለት ሺህ ሰዎች በቋሚነት በቀን አንድ ጊዜ እንደሚመገቡ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ባደረጉት ንግግር "አንዳችን ለሌላችን የተስፋ ብርሃን በመሆን መደጋገፍና መረዳዳት ይገባናል" ብለዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን የመደገፍ ተግባር ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው፤ የተስፋ ብርሃን የዜግነትን ክብር ጠብቆ ከምገባ ያለፈ ሌሎች ችግሮችም የሚፈቱበት ማዕከል እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በክፍለ ከተማው የሚገኙ የእለት ጉርስ ለማግኘት ለከበዳቸው ነዋሪዎች ተስፋና ብርታት መሆኑን የገለጹት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ ናቸው።
በክፍለ ከተማው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ወቅት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 98 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መታወቁን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 54 ሺህ ያህሉ እጅግ በከፋ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ እንደሚኖሩ አክለዋል።
የምገባ ማዕከሉ ለ54 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ይታያል ከነገ ጀምሮ በቋሚነት በየቀኑ ሁለት ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ከማዕከሉ ግንባታ በተጨማሪ ዓመቱን ሙሉ የምገባ ወጪውን ለመሸፈን ውል መግባታቸውን ገልጸዋል።
በማዕከሉ ግንባታ የተሳተፈው ዳሸን ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነዋይ በየነ በበኩላቸው ባንኩ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።