በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተሰራ በሠዓት እስከ 40 ኩንታል በቆሎ የሚፈለፍል ማሽን ለእይታ ቀረበ

239

ግንቦት 04/2013 (ኢዜአ)  በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተሰራና በሠዓት ከ30 እስከ 40 ኩንታል በቆሎ መፈልፍል የሚችል ማሽን በኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እይታ ቀርቧል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ዘመናዊውን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ጄላ አሉቶ ቀበሌ ትናንት ለአርሶ አደሮች ምልከታ አቅርቧል፡፡   

ማሽኑ አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት በቆሎ ለመፈልፍል የሚያወጣውን ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ የሚቀንስና የምርት ብክነትን ለመከላከል የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃይሉ ዳዲ ማሽኑ ለአርሶ አደሩ የሚያስገኛቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አስረድተዋል፡፡

በሠዓት ከ30 እስከ 40 ኩንታል በቆሎ የመፈልፈል አቅም ያለው ማሽኑ በአገር ውስጥ የተመረተ በመሆኑ አርሶ አደሩ በአነስተኛ ወጪ በመግዛት ሊጠቀምበት የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለማሳያ በቀረበው ማሽን ላይ አርሶ አደሮች የሚሰጡትን አስተያየት እንደ ግብዓት በመጠቀም ማሽኑ ከዚህ በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑንም ነው ዶክተር ሃይሉ የገለጹት።

በቀጣይም ማሽኑን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በመውሰድ ለአርሶ አደሮች የሚያሳዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ጀማል ሃጂ በበኩላቸው ማሽኑ አርሶ አደሩ ጋር ሲደርስ የበቆሎ ምርት ጥራትን የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡

ተቋማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱና ችግሮቹንም እንዲፈቱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኑም ከኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ማሽኑን ቢያገኙ በቆሎ ለመፈልፈል የሚያወጡትን ከፍተኛ ጉልበት እንደሚያስቀርላቸው ገልጸዋል፡፡

መንግስት ማሽኑ ተባዝቶ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተሰራውን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኑ ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም