የኢድ አልፈጥርን በዓልን ስናከብር ከኮሮና በመጠበቅና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል- ምክር ቤቱ

1217

ሐረር፤ ግንቦት 3/ 2013(ኢዜአ) የኢድ አልፈጥርን በዓልን ስናከብር እራስን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ቶፊቅ አብደላ ተናገሩ።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉን  ፖሊስ አስታውቋል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤በዓሉን ስናከብር አቅመ ደካሞችን፣ወላቹቻቸውን ያጡ ህጻናትና ሌሎችም ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል

በተለይ ህዝብን በማጋጨት የራሳቸውን ድብቅ  የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት  የሚሯሯጡ  ሃይሎችን ተግባር ምዕመናኑ ነቅተው  በመጠበቅ መከላከል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ጸረ ሰላም ሃይሎች የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ወጣቱን መጠቀሚያ ማድረግ የዕለት ተዕለት  ተግባራቸው በመሆኑ ወጣቱም ይህን በመገንዘበ አካባቢውን  በንቃት  መጠበቅ  እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

በሶላትና በሌሎች ቦታዎች በሚከናወኑ የበዓሉ ስነስርዓት ወቅት  ምዕመናኑ ከአስከፊው የኮሮና ቫይረስ እራሱን ለመጠበቅ  የመከላከያ መመሪያዎችን መተግበር እንዳለበትም አሳስበዋል።

1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥርን በዓል በክልሉ   ያለአንዳች የፀጥታ ችግር  ለማክበር  አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል  መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጃቢር አሊዩ አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ሃይማኖትን ከሃይማኖትና ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ሲሰሩ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን አስቀድሞ በመቆጣጠር ማክሸፍ መቻሉን አውስተዋል፡፡

የኢድ አልፈጥርን በዓል በሰላም እንዲከበር ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ  ሌሎች የጸጥታ  አካላት ጋር ተቀናጅቶ  የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት በኬላዎችና በሁሉም የከተማው ስፍራዎች እየተጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም ጸረ-ሰላም ሃይሎችን በማጋለጥ የሀገሩንና አካባቢውን ደህንነት  ለማስከበር የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡