የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል የፖሊስ ግብረ ኃይል ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

153

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል የፖሊስ ግብረ ኃይል ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስምምነቱን ከፖሊስ ዩኒቨርሲቲና ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር ነው የተፈራረመው፡፡

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ እንዳሉት የስምምነት ሰነዱ በተለይም ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዙ ስራዎችን ለመስራት ያስችላል፡፡
የስምምነት ሰነዱ በኢትዮጵያ ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም የተጠናከረ ስራ ለመስራት ይረዳል ተብሏል፡፡


ይህ ስምምነት በተቋማቱ መካከል የቴክኒክ እና ተግባር ተኮር ትብብርን በማጠናከር በአገሪቱ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ተነሳሽነት ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ዲና ጋይሌ ስምምነቱ ጽህፈት ቤቱ በተለይ በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን እገዛ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች ላይ የሚደርስን ማንኛውም አይነት ጥቃት መዋጋት የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ፅህፈት ቤት አስፈላጊ የሆነውን የቴክኒክ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የተፈራረምነው የትብብር ሰነድ በሴቶች ላይ የሚደርስን ማንኛውን አይነት ጥቃት ለመቆጣጠር በቂ የሆነ አቅም ለመገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መስፍን አበበ እንዳሉት ስምምነቱ የፖሊስ አባላት የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና በመስጠት የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡


የፌዴራል እና የክልል ፖሊሶች በሴቶች ላይ የሚደርስ ማንኛውንም አይነት ፆታዊ ጥቃትን ለመዋጋት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡


ተግባራቶቹ የጥቃት ወንጀሎችን መመርመር እና የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ለምርመራ እርዳታ ወደ ጤና ተቋማት መላክን ይጨምራል፡፡


ሆኖም መረጃዎች እንደሚሳዩት ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና ከተከሰተም በኋላ አስተማማኝ የሆነ የህግ ከለላ ለመስጠት በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ተጨማሪ የፖሊስ አባላት ያስፈልጋሉ፡፡


ስምምነቱ በሴቶች ጥቃት ዙሪያ ፖሊሶች ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው የሚረዱ ስልጠናዎችን ለመስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡


የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዘላለም መንግስቴ እንደተናገሩት ግጭቶችን ተከትሎ በሴቶች ፣ህጻናት እና ወጣቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ፖሊስ ጠንካራ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ሴቶች እና ህጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃት ባደረሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝና እና ከሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ 

የተፈረመው ሰነድ በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሴቶችን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም