ኢትዮ ቴሌኮም "ቴሌ ብር" የተሰኘ አዲስ የክፍያ አገልግሎት አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም "ቴሌ ብር" የተሰኘ አዲስ የክፍያ አገልግሎት አስጀመረ

ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም "ቴሌ ብር" የተሰኘ አዲስ የክፍያ አገልግሎት አስጀመረ።
በመርሃ- ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
"ቴሌ ብር" የተሰኘው አዲሱ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ምቹ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ እና መገበያያ ዘዴ ነው።
ይህም ደንበኞች የሞባይል ስልካቸውን ተጠቅመው ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዢ እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑ ተግልጿል።
አገልግሎቱ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ገንዘብ ለመላክ፣ ለመቀበል እና ለእቃ ግዢ አገልግሎቶች ይውላል።
ከእነዚህ በተጨማሪ እንደ ትምህርት ቤት፣ የውሃና ኤሌክትሪክ እንዲሁም በድርጅቱ ለሚቀርቡ አየር ሰዓትና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ክፍያን በስልክ ለመፈጸም ያስችላል ተብሏል።
ይህም ዘመናዊ የክፍያና የመገበያያ አገልግሎት አገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ የስልክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።