ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ፆም ወር ያሳየውን የመረዳዳት እሴት አጠናከሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

81

ሀዋሳ ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ ረመዳን ፆም ወር ያሳየውን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴት አጠናክሮ እንዲቀጠል ጥሪ ቀረበ።

1ሺህ 442ኛውን  የኢድ አልፈጥር በዓልን በማስመልከት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርአቶ ርስቱ ይርዳው  ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚሁ መልዕክታቸው እንዳሉት፤ህዝበ ሙስሊሙ በፆሙ ወር  ለሀገሪቱ ህዝብ ሰላም እና አንድነት በመጸለይ በይቅርባይነት መንፈስ ሀይማኖታዊ አስተምህሮቶችን ሲተገብር ቆይቷል።

ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመደጋፍና የመረዳዳት ባህላዊ እሴቶችን በማጠናከር ለአንድነት ያለውን ድርሻ ከግምት በማስገባት በሌላውም ጊዜ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በየአካባቢው ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ፣ በጤና ችግር ውስጥ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን መርዳትና ማገዝ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርኝሽ ባህሪውን በመቀየር በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ የብዙዎችን ህይወትእየነጠቀ በመሆኑ ህዝበ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት  ጥንቃቄ ሊያደርግ  እንደሚገባም አሳስበዋል።

አሁን ላይ አገራችን ከውስጥና ውጭ በተደቀኑፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መላው የክልሉና የሀገሪቱ ህዝቦች እነዚህ ጠላቶች የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና ለማስተጓጎል እየሠሩ መሆናቸውን በመገንዘብ መከላከል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችንና ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዳይጠናቀቁ የተለያዩ ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን ህዝቡ  ማጋለጥ አለበት ብለዋል።

አንዱን በአንዱ ላይ ለማነሳሳትና ህዝብን ለመከፋፈል የሚጥሩ ሃይሎች ልፋታቸውን ከንቱ ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውም አቶ ርስቱ ጠቁመዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የበኩሉንሚና እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም