በድሬዳዋ የኢድ አልፈጥር መስገጃ ስፍራ የክርስትና እምነት ተከታዮች አፀዱ

108

ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 3/2013 ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮችና የቤተክርስቲያን አመራሮች የኢድ አልፈጥር መስገጃ ሜዳን ዛሬ አፀዱ።

 ይህ በጎ ተግባር የድሬዳዋን ዘመን ተሻጋሪ የአንድነትና የአብሮነት ፅናት መሳያ በመሆኑ ሊጠበቅና ሊጠናከር እንደሚገባ ተመልክቷል።  

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት  ኃላፊ  ሊቀትጉሃን ማትያስ በቀለ ባደረጉት ንግግር ፤ የድሬዳዋ የፍቅርና የህብረት ዘመን  ተሸጋሪ እሴትን ለማጎልበትና ወንድማማችነትን ለማጽናት የኢድ መስገጃን ማጽዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ድሬዳዋ የተለያዩ እምነት ተከታዮችና ብሔር ብሔረሰቦች መዲና የመሆኗን እውነታ ለትውልድ ለማስተማር የየአብያተ ክርስቲያን አመራሮችና ምዕመናን አጋርነታቸውንና  ወንድማማችነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡

በክርስትናና እስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መካከል ግጭት በመፍጠር የተደበቀ ሀገርን የመበጥበጥና የፖለቲካ አጀንዳን የማሳካት ጉዳይ ድሬዳዋ ላይ እንደማይሳካ ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ  አስተዳደር ወንጌላውያን የአብያተ ክርስቲያናት  ህብረት አመራር ወንድም  ሚኪያስ ታዬ በበኩላቸው፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ በዘላቂነት ለመጠበቅ  ህዝቡ ዘብ ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች አመራሮችና ምዕመናን በሙሉ ያላቸውን  የጠበቀ ህብረትና አንድነትና ወንድማማችነትን ለመግለፅ የኢድ ሜዳን በማስተካከል ተግባር ላይ በፍቅር መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ሼህ አብደላ አህመድ በራርቲ እንደተናገሩት፤ ዛሬ የተካሄደው የፅዳት ዘመቻ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘመን የዘለቀ ህብረትና አንድነት መገለጫ ነው፡፡

ይህን አንድነት፣ ህብረትና ፍቅር ለመናድና በእምነቶች መካከል ችግር ለመፍጠር  የሚጠነሰስ ሴራ ቦታ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

የትኛውም ድብቅ ተልዕኮ በተቀናጀ መንገድ ይከሽፋል ብለዋል፡፡

በምከር ቤቱ የመስጂድና የአውቃፍ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ ኢብራሂም ሁሴን በበኩላቸው ፤ክርስቲያኖች ለእስልምና እምነት ተከታዮች ላሳዩት  ህብረትና ፍቅር  ምስጋናቸውን  አቅርበው ይህ ህብረት ዘመን ይሻገራል ብለዋል

የ1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጠር በዓል ላይ የሚገኙ ምዕመናን የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮል ሙሉ በሙሉ የሚያከብሩ መሆናቸውንና የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስፈላጊውን  ጭንብልና  የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ማድረጉንም ገልፀዋል፡፡

በፅዳት ዘመቻው ላይ የፍትህና የፀጥታ እንዲሁም የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም