በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የነበረው መከፋፈል የቤተ ክርስቲያንን ጉባዔ ባከበረ መልኩ ተፈቷል ፡- የኃይማኖት አባቶች

113
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የነበረው የሲኖዶስ መከፋፈል የቤተ ክርስቲያንን ጉባዔ ባከበረ መልኩ መፈታቱን የኃይማኖት አባቶች አስታወቁ። በስደት የቆዩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ 4ኛ ፓትርያርክ ዘኢትዮዽያን ለመቀበል በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በነበረው ሥነ ስርዓት ላይ የኃይማኖት አባቶች እርቁ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ተከትሎ የተከናወነ በመሆኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ "እነሆ ወንድሞች ሰብሰብ ብለው ቢቀመጡ መልካም ነው" የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጠቅሰው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስና እሳቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን  ችግር ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት ታሪክ ትልቅ ባለሟል ናቸው" በማለት የመንግስት ድጋፍ ተጨምሮበት እርቀ ሰላሙ በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም ምንጭ የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ ተጠብቆ እንዲኖር በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንመራዋለን የሚል እምነት አለንም ብለዋል ቅዱስነታቸው አቡነ ማቲያስ። ኢትዮጵያ ዛሬም ጀግኖችና ታሪክ የሚሰሩ ትውልዶች እንዳሏት የገለጹት አቡነ ማቲያስ የቆየውን የልዩነት ታሪክ የሚያስቀሩ የሥራ ውጤቶችን እየተመለከትን ነው ብለዋል። የባህርዳርና ምዕራብ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው ለእርቀ ሰላሙ ምክንያት ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና አቅርበዋል። ሌሎች አባቶችም የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት ሳይለቅና ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እርቁን ያመጡልን እግዚአብሔር የመረጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "ቤተ ክርስቲያኗን ከመከፋፈል አድነዋታል" ብለዋል። ለ26 ዓመታት የነበረውን የቤተ ክርስቲያኗ መከፋፈል ችግር ከሐይማኖት አባቶች በላይ ብርቱ ጥረት በማድረግ ችግሩ እንዲፈታ ያደረገው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው መንግሥት ነው ብለዋል የሐይማኖት አባቶቹ። ካለፈው ትምህርት ወስደን ይህን መሰል የመከፋፈል ችግር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ መድገም የለብንም በማለትም በሥነ ስርዓቱ ላይ የታደሙት የሐይማኖት አባቶች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም