የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

89
ድሬዳዋ  ሀምሌ 25/2010 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ለአዲሱ በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ። ዛሬ በተጠናቀቀው የምክር ቤቱ 5ኛ ዓመት 39ኛ መደበኛ ጉባኤም ምክር ቤቱ ከበጀቱ በተጨማሪ ሹመትና አዋጅንም አጽድቋል። የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እንዳስታወቀው በጀቱ በገጠርና በከተማ በመተግበር ላይ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና መሠረታዊ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች በመመለስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልሰመድ መሐመድ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የበጀት ቀመር መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት የተመደበው በጀት የሁለተኛውን የእድገትና የትራንስፎርሽን የዘንድሮ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ያስችላል። በገጠርና በከተማ እየተከናወኑ ያሉትን ጨምሮ የዘንድሮ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ የህዝቡን ጥያቄ ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስ እንደሚያስችልም አመልክተዋል፡፡ አቶ አብዱልሰመድ እንዳሉት ከፌደራል መንግስት ለአስተዳደሩ የተመደበው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማና ከአስተዳደሩ የሚሰበሰብ ገቢን ጨምሮ ለዘንድው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 721 ሚሊዮን  ብር በላይ በጀት ተመድቧል፡፡ "ከተመደበው በጀት 49 ነጥብ 1 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶችና ለዘላቂ ልማት ግብ ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን ጤና፣ ትምህርት መሠረተ ልማት፣ የመጠጥ ውሃና የሥራ ዕድል ፈጠራ ልማቶች የበጀቱን 75 በመቶ የሚጠቀሙ ሲሆን ይህም ለድህነት ቅነሳው ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል" ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በጀቱ በአግባቡ መደልደሉንና ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ እንደሚሰጥ እምነታቸውን ገልጸው፣ ለተግባራዊነቱ የቁጥጥርና የክትትል ሥራቸውን እንደሚያጠናክሩ አስረድተዋል፡፡ ምክር ቤቱ ከበጀቱ በተጨማሪ የድሬዳዋ አስተዳደር ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በተዘጋጀ አዋጅ ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ ያፀደቀ ሲሆን ዶክተር ደራራ ሁቃንም የድሬዳዋ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማናጅመንት ቢሮ ኃላፊ በማድረግ ሾሟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም